Fana: At a Speed of Life!

5 ስራ አስኪያጆችን ጨምሮ 9 ተከሳሾች ከ87 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ማድረስና ሰነዶችን በማጥፋት የሙስና ወንጀል ክስ ቀረበባቸው

አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) 2 የባንክ ቅርጫፍ ስራ አስኪያጆች እና 3 የግል ድርጅት ስራ አስኪያጆችን ጨምሮ 9 ተከሳሾች ከ87 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ማድረስና ሰነዶችን በማጥፋት የሙስና ወንጀል ክስ እንደቀረበባቸው የፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በተከሳሾቹ ላይ በየተሳትፎ ደረጃ መጠን ጠቅሶ 6 ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክሶችን እንዳቀረበባቸው ተገልጿል፡፡

ክሱ የቀረበው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው ተብሏል።

ተከሳሾቹ 1ኛ የወጋገን ባንክ ሀያት ቅርጫፍ ስራ አስኪያጅ የነበሩት መስፍን ገ/መድህን እና 2ኛ ሲኤሚሲ ቅርጫፍ ስራ አስኪያጅ ሀይላይ ገ/ሚካኤል መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

3ኛ እና 4ተኛ ተከሳሾች የኮንኮርዲያ ትሬዲንግ ስራ አስኪያጆች የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ስዩምና አቶ ሄኖክ ፈለቀ እንዲሁም 5ኛ ተከሳሽ ኮንኮርዲያ ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር ናቸው፡፡

6ኛ ተከሳሽ የአዲስ ዋይ ቴክኖሎጂ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍሬው ዘውዱ፣ 7ኛ ተከሳሽ አቶ አብዱልቃድል አንዋር የፍሬው ዘውዱ ወኪል እንዲሁም 8ኛ ተከሳሽ የኢኤስ ቢኤች ትሬዲንግ ስራ አስኪያጅ ፍቅረማርያም ገብሩ እንዲሁም 9ኛ ተከሳሽ ኢኤስ ቢኤች ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር ናቸው ተብሏል፡፡

1ኛ ተከሳሽ የባንኩ ስራ አስኪያጅ ሆኖ ሲሰራ ከኮንኮርዲያ ትሬዲንግ ማህበርና የማህበሩ ስራ አስኪያጆች ከሆኑት ከ3ኛ እና ከ4ኛ ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር ወንጀሉን እንደፈጸሙት ተገልጿል፡፡

የባንኩን መመሪያ በመተላለፍ የተሰጠውን ስልጣን ያለአግባብ በመገልገል በነሀሴ 12 ቀን 2013 ዓ/ም ለ3ኛ፣ 4ኛ እና ለ5ኛ ተከሳሶች ለያንዳንዳቸው የ6 ሚሊየን 500 ሺህ ብር ሲፒዮ አዘጋጅቶ እንደሰጠ ተጠቅሷል፡፡

በተለያዩ ቀናቶች 34 ሚሊየን 617 ሺህ 700 ብር ገንዘብ ሲፒዮ በአንደኛ ተከሳሽ ተዘጋጅቶ ለ6ኛ እና ለ7ኛ ተከሳሾች የተሰጠ መሆኑን ዐቃቤ ሕግ ጠቅሶ÷ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።

2ኛ፣ 3ኛ፣ 4ኛ፣ እና 5ኛ ተከሳሾች በቀረበባቸው የሙስና ወንጀል ክስ እንደተመላከተው÷ 2ኛ ተከሳሽ ስራ አስኪያጅ ሆኖ ሲሰራ ከባንኩ መመሪያ ውጪ 32 ሚሊየን 500 ሺህ ብር ሲፒዮ አዘጋጅቶ እንደሰጠ ተገልጿል፡፡

በ2ኛ፣ በ8ኛ እና በ9ኛ ተከሳሾች ላይ በቀረበባቸው ክስ እንደተመላከተው ÷ 2ኛ ተከሳሽ ባዘጋጀው የ14 ሚሊየን ብር ሲፒዮ 8ኛ እና 9ኛ ተከሳሾች በመውሰድ የአየር ሰዓትና የሚፋቅ የሞባይል ካርድ ከኢትዮ ቴሌኮም ግዢ ፈጽመዋል፡፡

ተከሳሾቹ ከአሰራር ውጪ የተዘጋጀ ሲፒዮ በመውሰድና 87 ሚሊየን 617 ሺህ 700 ብር ጉዳት ማድረስ ሙስና ወንጀል ተከሰዋል።

በተጨማሪም 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሶች÷ በተለያዩ ቁጥሮች የተመዘገቡ ስድስት ሲፒዮዎችን በማጥፋት የህዝባዊ ድርጅት ሰነዶችን በማጥፋት በባንኩ ላይ ከባድ ጉዳት በማድረስ ሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።

የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለየካቲት 11 ቀን 2015 ዓ/ም የተቀጠረ ሲሆን÷ የፌደራል ፖሊስ ላልቀረቡ ቀሪ አምስት ተከሳሾች መጥሪያ እንዲያደርስና በቀጣይ ቀጠሮ ተከሳሾቹ እንዲቀርቡ ታዟል።

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.