ኔዘርላንድስ የኤሌክትሪክ ባቡሮቿን ሙሉ በሙሉ በነፋስ ሃይል ማንቀሳቀስ ጀመረች

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኔዘርላንድስ የኤሌክትሪክ ባቡሮቿን ቡሉ በሙሉ በነፋስ ሃይል ማንቀሳቀስ መጀመሯን ይፋ አድርጋለች።

ሀገሪቱ የባቡሮቿን የሃይል ፍጆታ ከነፋስ ሃይል ለማድረግ ከአንድ ዓመት በፊት ነበር ያቀደችው፡፡

የደች የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የኤሌክትሪክ ባቡሮቹ የነፋስ ሃይል ማመንጫውን እንዲጠቀሙ ያደረገው፥ ከሀገሪቱ የሃይል አቅርቦት ድርጅት ኤኔኮ ጋር በደረሰው ስምምነት መሆኑ ተነግሯል፡፡

ለአስር ዓመት የሚቆይ የአገልግሎት ስምምነትም በሁለቱ ተቋማት መካከል ከሁለት ዓመት በፊት ተፈርሞ ነበር፡፡

ሁለቱ ተቋማት በጎርጎሮሳውያኑ 2018 በኔዘርላንድስ የሚገኙ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ባቡሮችን የሃይል ፍጆታ ሙሉ በሙሉ በነፋስ ሃይል ለመቀየር ነበር ያቀዱት፡፡

ነገር ግን ከታቀደው አንድ ዓመት ቀድሞ በ2017 ጥር ወር መተግበሩን የደች የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ቃል አቀባይ ቶን ቡን ተናግረዋል፡፡

በኔዘርላንድስ የኤሌክትሪክ ባቡሮች በአንድ ቀን ብቻ በሚያደርጓቸው 5 ሺህ 500 ጉዞዎች እስከ 600 ሺህ ተሳፋሪዎችን የሚያጓጉዙ ሲሆን በዚህም ኔዘርላንድ ከዓለም ቀዳሚ ትሆናለች ነው የተባለው፡፡

ባቡሮቹ በሚያደርጉት ጉዞ በዓመት ውስጥ 1 ነጥብ 2 ቢሊየን ኪሎ ዋት የኤሌክትክ ሃይልን ይጠቀማሉ፡፡

ይህ ሃይል የአምስተርዳም ነዋሪዎችን በተመሳሳይ ጊዜ ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ፍጆታ መሸፈን እንደሚያስችል ነው የተገለፀው።

አሁን ላይ የነፋስ ሃይሉ ባቡሮቹን 120 ማይሎችን በአንድ ሰዓት ማስጓዝ እንደሚያስችል ተነግሯል፡፡

የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅቱ ባቡሮቹ አሁን የሚጠቀሙትን የሃይል ፍጆታ በ2020 የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት በ35 በመቶ ለመቀነስ አቅዷል፡፡

ይህም ባቡሮቹ በትንሽ የሃይል መጠን ረጅም ርቀቶችን እንዲጓዙ ያስችላቸዋል ነው የተባለው፡፡

 

ምንጭ፡- ዘጋርድያን

በምህረት አንዱዓለም

android_ads__.jpg