አይፎን 8 ገመድ አልባ ሀይል መሙያ (ቻርጀር) እንደሚኖረው ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አፕል ከወራት በፊት አይፎን 7 ስማርት ስልኩን ለገበያ ማቅረቡ ይታወሳል።

የአይፎን አድናቂዎች በዚህ አመትም የአዲሱን አይፎን 8 ስማርት ስልክ ለገበያ መቅረብ እየተጠባበቁ ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2007 ጥር 9 በስቲቭ ጆብስ የተመሰረተው አፕል 10ኛ አመቱን ይዟል።

አፕል 10ኛ አመቱን ሲያከብር ከዚህ ቀደሞቹ በበለጠ እጅግ ዘመናዊ ነው የተባለውን ስማርት ስልክ (አይፎን 8) ለገበያ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።

የእንግሊዙ ሚረር ድረ ገፅም ስለ አይፎን 8 የተሰሙ ጭምትምታዎችን ይዞ ወጥቷል።

አይፎን 8 ሶስት የስክሪን ስፋት ይዞ ይመጣል። (ባለ 5፣ 4 ነጥብ 7 እና 5 ነጥብ 5 ኢንች)

የጃፓኑ ማክ ኦክታራ ብሎግ ሶስቱም ሞዴሎች ተመሳሳይ የጥራት ደረጃ ስፔስፊኬሽን እንደሚኖራቸው ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

አፕል ብዙ ጊዜ ስማርት ስልኮቹን ለገበያ የሚያቀርበው በመስከረም ወር የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት እና በገና ሰሞን ነው።

አይፎን 8 ስማርት ስልኩንም እንደተለመደው በመስከረም ወር ሁለት ሳምንታት ለገበያ ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚያም ቀደም ብሎ በሰኔ ስልኩን ለገበያ ሊያውል ይችላል።

የአፕል አይፎን 8 እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ኪስን የሚጎረብጥ ዋጋ እንደሚወጣለት ይጠበቃል፤ ነገር ግን በጣም የተጋነነ እንደማይሆን ተገልጿል።

32 ጊጋ ባይት የመያዝ አቅም ያለው አይፎን 7 559 ፓውንድ፤ ባለ 64 ጊጋ ባይቱ ደግሞ 719 ፓውንድ ሲሸጡ እንደነበር ይታወቃል።

የአይፎን 8 ዋጋም ከዚህ በተወሰነ ደረጃ መጨመሩ እንደማይቀር ነው ነው የተነገረው።

አፕል አዲሱ ስልኩ ሙሉ በሙሉ የመስታወት ሽፋን እንዲኖረው ተገልጿል።

የኬ ጂ አይ ሴኩሪቲስ ተንታኙ ሚንግ ቺ ኩኦ፥ የአሜሪካው ኩባንያ የአይፎን ስማርት ስልኮችን ሽፋን በአልሙኒየም ሳይሆን በመስታወት ይሰራል ብለዋል።

አይፎን 8 ይዟቸው ይመጣሉ ተብለው ከሚጠበቁ ጉዳዮች መካከል በገመድ አልባ ሀይል የሚሞላ መሆኑ ይጠቀሳል።

ሶስቱ ሞዴሎች 32 ጌጋ ባይት፣ 128 ጊጋ ባይት እና 256 ጊጋ ባይት የመያዝ አቅም ይኖራቸዋል ተብሏል።

አይፎን 7 አንድ ሜትር ጥልቀት ባለው ውሃ ውስጥ ለ30 ደቂቃ ያህል ውሃ ሳያስገባ መቆየት ይችላል።

አዲሱ አይፎን 8 እንዲሁ ውሃ የማያስገባ ይሆናል ተብሏል።

 

ምንጭ፦ www.mirror.co.uk/

 

 

በፋሲካው ታደሰ

 

android_ads__.jpg