ጨረቃ በሚቀጥለው ዓመት የሞባይል ዳታ ኔትወርክ ሊተከልላት ነው

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 11 ፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በፈረንጆች 2018 ዓመት ጨረቃ የራሷ የሆነ የሞባይል ዳታ ኔትወርክ እንዲኖራት ለማድረግ ማቀዱን መቀመጫውን ጀርመን ያደረገ የሳይንቲስቶች ቡድን አስታወቀ፡፡

የኔትወርክ ጣያውን መተከል ተከትሎ ሁለት የጨረቃ መረጃ ሰብሳቢ ተሸከርካሪዎች የአሜሪካ የአፖሎ ፕሮግራም አካል በመሆን፥ በኤለን መስክ ስፔስ ኤክስ ፋልከን-9 ሮኬት ወደ ስፍራው ያመራሉ ተብሏል፡፡

ፓርት ታይም ሳይንቲስትስ የተሰኘው ኩባንያ መርሃ ግብሩን በሚቀጥለው ዓመት በመተግበር የመጀመሪያው የንግድ ኩባንያ ለመሆን አልሟል፡፡

መቀመጫውን በርሊን ያደረገው ይህ ኩባንያ ከቮዳፎን ጋር በመሆን ነው ዕቅዱን ለማሳካት የተነሳው፡፡

moon.jpg

ጨረቃ ላይ ኔትወርክ የሚያመጡ ሁለት ተሸከርካሪዎችን ወደ ስፍራው ለመላክ አቅዷል፡፡

ይህም ጨረቃ ላይ ያሉት ተሸከርካሪ መረጃ ሰብሳቢዎች በቀላሉ መሬት ላይ ካሉ ማዕከላት ጋር መልዕክት እንዲለዋወጡ ለማስቻል ነው፡፡

የሰው ልጅ ከመሬት ውጭ ባሉት ዓለማት ይኖር ዘንድ ወይም እንዲያውቃቸው ለማድረግ ጨረቃን በመሳሰሉ የህዋ አካላት ላይ መሰረተ ልማት መገንባት ታስቧል ይላሉ የፓርት ታይም ሳይንቲስቶች ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሮበርት ቦሄም፡፡

በጨረቃ ላይ የሚሰራው የሞባይል ዳታ ኔትወርክ ጣቢያ ኤል ቲ ኢ የተሰኘ ቴክኖሎጂን ይጠቀማል ተብሏል፤ ይህ ቴክኖሎጂ በዓለማችን ባሉ በቢሊየን የሚቆጠሩ ስልኮች ላይ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ነው፡፡

አሊና የተባለቺው መረጃ ሰብሳቢ ተሸከርካሪ በጨረቃ ላይ በመዞር በተተከለው የሞባይል ዳታ ኔትወርክ አማካኝነት በካሜራ እና በሌሎችም የተቀዱ መልዕክቶችን ወደ መሬት ትልካለች፡፡

ኤል ቲኢ ቴክኖሎጂን መጠቀም የተፈለገው በትንሽ ኃይል ብዙ መልዕክቶችን ማስተላለፍ የሚያስችል በመሆኑ ነው፡፡

ምንጭ፡-0www.wired.co.uk