“ኤሮሞቢል” የመጀመሪያዋን በራሪ ተሽከርካሪ እውን አድርጎ ከገዢዎች ትእዛዝ መቀበል ጀምሯል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) “ኤሮሞቢል” የመጀመሪያውን በራሪ ተሽከርካሪ እውን አድርጎ ለእይታ አቅርቧል።

ከሳምንታት በፊት ነበር መቀመጫውን ስሎቫኪያ ያደረገው ኤሮሞቢል የሰራውን በራሪ ተሽከርካሪ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት የሽያጭ ቅድመ ትእዛዝ መቀበል እንደሚጀምር አስታውቆ የነበረው።

ታዲያ ኩባንያው ቃሉን ጠብቆ የመጀመሪያውን በራሪ ተሽከርካሪ ይዞ የመጣ ሲሆን፥ በራሪውን መኪና መግዛት የሚፈልግ ሰውም የቅድመ ሽያጭ ትእዛዝ መፈፀም እንደሚችል አስታውቋል።

አዲሱ የኤሮሞቢል በራሪ ተሽከርካሪ በትናንትናው እለት ለእይታ የቀረበ ሲሆን፥ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ያለው ማንኛውም ሰው ተሽከርካሪውን ማዘዝ ይችላል ተብሏል።

መግዛት የሚፈልጉ ሰዎች መኪናውን አሁን ለግዢ ይዘዙ እንጂ በራሪው መኪና እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2020 በፊት እጃቸው እንደማይገባ ነው የተነገረው።

ለየት ያለ ዲዛይን አለው የተባለው ይህ የኤሮሞቢል በራሪ መኪና፥ ስንፈልግ አየር ላይ ማብረር ስንፈልግ ደግሞ ልክ እንደ መኪና በመንገድ ላይ መንዳት እንችላለን ነው የተባለው።

aeromobil_1.jpg

በውስጡ ከአውሮፕላን መቆጣጠሪያ ጋር የሚመሳሰል ስርዓት ያለው በርካታ ስክሪኖች የተገጠሙለት ሲሆን፥ ውስጡ ያለው ሰው ሲበር አሊያም ጎዳናላይ ሲያሽከረክር የሚጠቀምበት ነው።

“ኤርሞቢል” የተባለው ይህ በራሪ ተሽከርካሪ ከመኪናነት ወደ በራሪ አውሮፕላንነት ለመቀየር 3 ደቂቃ ብቻ እንደሚፈጅበትም ተነግሯል።

ተሽከርካሪው በምድር ላይ በሚነዳበት ጊዜ በሰዓት እስከ 160 ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችል ሲሆን፥ አየር ላይ በሚበርበት ጊዜ ደግሞ በሰዓት እስከ 360 ኪሎ ሜትር እንደሚበር ነው የተነገረው።

ምንጭ፦ https://fossbytes.com