ኤች.ቲ.ሲ U11 የተባለ የሚጨመቅ ስማርት ስልክ አቅርቧል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) ኤች.ቲ.ሲ በስማርት ስልክ ዓለም በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነና በእጃችን የሚጨመቅ ስማርት ስልክ አቅርቧል።

U11 የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ የኤች.ቲ.ሲ ስማርት ስልክ በአራት አቅጣጫዎች መጭመቅ የሚቻል ሲሆን፥ ይህም ራስን በራስ ፎቶ ግራፍ ለማንሳት (ሰልፊ) እና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚጠቅመን ነው ተብሏል።

የስማርት ስልኩ ውሃን ወደ ውስጥ እንዳያስገባ ተደርጎ የተሰራ ሲሆን፥ ከፍተኛ የድምጽ ጥራት ያለው “ሀይ ሬስ ኦዲዮ እና ቡም ሳውንድ ስፒከር” ተገጥሞለታል።

5 ነጥብ 5 ኢንች የስክሪን ስፋት ያለው ኤች.ቲ.ሲ U11 ስማርት ስልክ፥ ከወደቀም በቀላሉ የማይሰበር “ጎሪላ ግላስ 5” ስክሪን እንደተገጠመለትም ተነግሯል።

12 ሜጋ ፒክስል የምስል ጥራት ያለው ባለ ሶስት አነስተኛ ሌንሶች ካሜራም በስማርት ስልኩ ጀርባ ላይ የተገጠመለት መሆኑን ኤች.ቲ.ሲ ኩባንያ አስታውቋል።

ኤች.ቲ.ሲ U11 ከ4 ጊጋ ባይት እስከ 6 ጊጋ ባይት የሚደርስ ራም እና ከ64 ጊጋ ባይት እስከ 128 ጊጋ ባይት የሚደርስ የውስጥ የመረጃ መያዣ ቋት (ስቶሬጅ) እንዳለውምተገልጿል።

squeez_1.png

ስልኩን በምንጨምቅበት ጊዜም የተለያዩ አገልግሎቶች ይከፈቱልናል የተባለ ሲሆን፥ ከነዚህም ውስጥ በቀላሉ ፎቶ ግራፍ ማንሳት አንዱ ነው።

እንዲሁም ስልኩን ረዘም ላለ ጊዜ የምንጨምቅ ከሆነ ደግሞ የስማርት ስልኩን ካሜራ ወደ ፊት እና ወደ ኋላ ለማዞር ይጠቅመናል።

ስማርት ስልኩ በሰኔ ወር አካባቢ ለገበያ ይቀርባል የተባለ ሲሆን፥ ከ700 እስከ 850 የአሜሪካ ዶላር የመሸጫ ዋጋ ተቆርጦለታል።

ምንጭ፦ www.huffingtonpost.co.uk