ህንድ ግዙፉን የኢንተርኔት መዛግብት ማከማቻ አገደች

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህንድ ዋይባክ ማሽን የተባለውን የኢንተርኔት መዛግብት ማከማቻ አገደች።

በሀገሪቱ የሚገኙ የኢንተርኔት አቅራቢ ድርጅቶች የኢንተርኔት መዛግብት ቋቱን ሰርዘውታል፡፡

የቀጥታ ኢንተርኔት ቋቱ ህንዳውያን ረጅም እድሜ ያላቸውን የኢንተርኔት መረጃዎች እና ከ302 ቢሊየን በላይ የመረጃ ዓይነቶችን ማግኘት የሚችሉበት መዛግብ ማከማቻ ነው፡፡

ተጠቃሚዎች የመረጃ ቋቱ በሀገሪቱ የቴሌኮሙዩኒኬሽን መስሪያ ቤት ትዕዛዝ እንዲዘጋ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ሆኖም የህንድ መንግስት የሰጠው ማስተባበያ እንደሌለ ነው መረጃዎች የሚያሳዩት፡፡

የህንድ የፕሬስና ማስታወቂያ ቢሮ ዳይሬክተር ሻምቡ ቾውዳሪ፥ ፍርድ ቤቶች እና የደህንነት መስሪያ ቤቶች የተወሰኑ ድረ ገፆች እንዲዘጉ ትዕዛዝ የሚያወርዱ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ምክንያታቸውን አያሳውቁም ብለዋል፡፡

በተወሰኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች የኢንተርኔት መዛግብት ቋቱ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ሊቋረጥ ይችላል በሚል ስጋትን ፈጥሯል፡፡

መቀመጫውን ሳን ፍራንሲስኮ ያደረገው የኢንተርኔት መዛግብት ቋት ስራ አስኪያጅ ክሪስ በትለር፥ ስለሁኔታው ምንም ዓይት ቅድመ እውቅና እንደሌላቸው እና የቋቱ መዘጋት ግራ እንዳጋባቸው ተናግረዋል፡፡

ህንድ ከአጠቃላይ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ህዝቧ 462 ነጥብ 1 ሚሊየን ያህሉ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡

ሀገሪቱ በኢንተርኔት ተጠቃዎች ቁጥር ከቻይና ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ብትቀመጥም በ2014 ቪሜኦ፣ ደይሊ ኔሽን እና ሌሎች 29 ታዋቂ ድረ ገፆች የፅንፈኛ ሃይሎችን አቋም ማሰራጫ ሆነዋል በሚል እንዲዘጉ ማድረጓ ይታወሳል፡፡

ምንጭ፡-ቢቢሲ