ፌስቡክ አዲስ የቪዲዮ አገልግሎት አስተዋወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ ፌስቡክ ከዩትዩብ እና የሌሎች የኢንተርኔት ቴሌቭዥን ዝግጅት አሰራጮች ጋር የሚያፎካክረው አዲስ የቪዲዮ አገልግሎት አስተዋውቋል።

የአዲሱ የፌስቡክ የቪዲዮ አገልገሎት “ወች (Watch)” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ሲሆን፥ በርካታ የአጫጭር የቪዲዮ ዝግጅቶችን (ሾው) በፌስቡክ ገጻችን ላይ የሚያቀርብለን ነው ተብሏል።

የፌስቡክ ተጠቃሚዎችም በቅርቡ በገጻቸው ላይ “Watch” የመክፈቻ አማራጭ ያገኛሉ የተባለ ሲሆን፥ በዚህም ቪዲዮዎችን መመልከት ይችላሉ ነው የተባለው።

ቪዲዮዎቹም ጓደኞቻችን በብዛት የሚመለከቱት ዝግጅትች (ሾው) ላይ ተመርኩዞ በአማራጭነት አንደሚቀረቡልን ተነግሯል።

በፌስቡክ ላይ ቪዲዮዎቹን በምንመለከትበት ጊዜ የሚጻፉ አስተያየቶችን መመልከት የምንችል ሲሆን፥ ቪዲዮውን ከሚመለከቱ ሰዎች ጋርም መገናኘት እና ሀሳብ መለዋወጥ ያስችልናል።

face_book_tv.png

አዲሱ የቪዲዮ አገልግሎት ሰዎች ያጋጠማቸውን ነገሮች እንዲጋሩ እና ስለተመሳሳይ ነገር የሚያስቡ ሰዎችን አንድ ላይ የማምጣት አላማ እንዳለው የፌስቡክ መስራች ማርክ ዙከርበርግ ተናግሯል።

“ወች (Watch)” የተባለው አዲሱ የቪዲዮ አገልግሎት በመላው ዓለም ላይ ከመለቀቁ በፊት መጀመሪያ ላይ አሜሪካ ውስጥ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ እንደሚለቀቅ ፌስቡክ አስታውቋል።

ምንጭ፦ www.bbc.com