የሩሲያ መረጃ ጠላፊዎች በአሜሪካ የደህንነት ተቋም ላይ ስለላ ሲያካሂዱ እንደነበር ተገለጸ

የእስራኤል የመረጃ ጠላፊዎች የሩሲያ መረጃ ጠላፊዎች ካስፔርሲኪ ሶፍትዌርን በመጠቀም በአሜሪካ ብሄራዊ የደህንነት ኤጀንሲ ላይ ስለላ ሲያካሂዱ ደርሰውባቸዋል ተብሏል።

ዋሽንግተን ፖስት እና ዘ ኒውዮርክ ታይምስ የሩሲያ የመረጃ ጠላፊዎች በአሜሪካ የደህንነት ተቋም ላይ በካስፐርስኪ የፀረ ቫይረስ ሶፍትዌር አማካኝነት የመረጃ ብርበራ መፈፀማቸውን የሚያሳይ መረጃ ይዘው ወጥተዋል።

ሩሲያውያኑ መረጃ ጠላፊዎች የመስሪያ ቤቱን ሚስጥሮች ሲያስሱ የተገኙት በእስራኤላውያን የመረጃ ጠላፊዎች መሆኑን ነው ጋዜጦቹ ያስነበቡት።

ለዚህም ማሳያ እስራኤላውያን የመረጃ ጠላፊዎች ከዚህ ቀደም ማለትም ከ2015 በፊት የአሜሪካ ብሄራዊ የደህንነት ኤጀንሲ የመረጃ ደህንነትን ለማስጠበቅ ውል ፈፅሞ በነበረው የሩሲያ ድርጅት ላይ ስለላ አካሂደው ነበር።

በዚህም ድርጅት ሩሲያ የምትታወቅበትን ካስፐርስኪ የፀረ ቫይረስ አምራች ኩባንያ ያበለፀገውን ሶፍትዌር ለመረጃ ጠለፋ ሲጠቀምበት እንደነበር ባደረጉት ብርበራ ደርሰውበታል ይላል የዘ ኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ።

በ2014 በሩሲያ የመረጃ መረብ ደህንነት ኩባንያ ላይ ለተፈፀመው የመረጃ መረብ ጥቃት እስራኤል ከጀርባ እንዳለችበትም ዘ ኒውዮርክ ታይምስ በዘገባው ጠቅሷል።

ሩሲያ የካስፐርስኪ የፀረ ቫይረስ ሶፍትዌርን በጎግል የመረጃ ማፈላለጊያ ውስጥ ሚስጥሮችን እንዲጠልፍ ለማድረጊያ ዓላማ ማዋሏን የእስራኤል መረጃ ጠላፊዎች ማረጋገጣቸውም በመረጃው ላይ ተጠቅሷል።

በዚህም ሶፍትዌሩ የአሜሪካ የደህንነት እና የስለላ ተቋማት የሚጠቀሙባቸውን ሚስጥራዊ ኮዶች ለመውሰድ እና ሰብሮ ለመግባት ዓላማ መዋሉ ነው የተነገረው።

የብሄራዊ ደህንነት ኤጀንሲው ዋነኛ የመረጃ መረብ ደህንነት ተቆጣጣሪ የነበረው ኩባንያ፥ ካስፐርስኪን በመጠቀም የኤጀንሲውን ሚስጥሮች ለሌላ አካል አስተላልፏል የሚል ውንጀላም ነው የቀረበው።

ካስፐርስኪ በፀረ ቫይረስ ሶፍትዌር በመላው ዓለም ቢያንስ በ400 ሚሊየን ኮምፒውተሮች ላይ ተግባራዊ ሆኗል።

ከዚህ ባለፈ ግን ስለሁኔታው በዝርዝር የሚገልፁ መረጃዎች አልወጡም።

ካስፐርስኪ በበኩሉ የፀረ ቫይረስ ሶፍትዌሩ ለተባለው የመረጃ ጠለፋ ዓላማ አልዋለም የሚል ማስተባበያ ሰጥቷል።

የአሜሪካ የሀገር ውስጥ የደህንነት ተቋም ሁሉም የመንግስት ተቋማት ካስፐርስኪን በፀረ ቫይረስ ሶፍትዌርነት እንዳይጠቀሙ ማዘዙም ይታወሳል።

ካስፐርስኪ ከኮምፒውተሮች ላይ ቫይረሶችን ለማስወገድ 'silent signatures' የተባለ ቴክኖሎጂን ይጠቀማል ተብሏል።

ይህን ቴክኖሎጂ መጠቀሙ ሌላ ፋይዳ አለው፥ ይኸውም በመረጃ ማፈላለጊያነት ሩሲያ የአሜሪካን የደህንነት ሚስጥሮች እንድትበረብር ማስቻል መሆኑ ነው የተነገረው።

 

 

 

 

ምንጭ፦www.neowin.net