ፌስቡክና ኢንስታግራም ትናንት ምሽት በአብዛኛው የዓለም ክፍል ተቋርጠው ነበር

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ የሆኑት ፌስቡክ እና ኢንስታግራም በትናንትናው ምሽት የመቋረጥ ችግር አጋጥሟቸው እንደበረ ተገለፀ።

ከሰዓታት በኋላ ግን ሁለቱም የማህበራዊ ትስስር ግረ ገጾች ወደ መደበኛ አገልግሎታቸው መመለሳቸው ነው የተነገረው።

ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ድረ ገጽ ኩባንያ ፌስቡክ፥ በዋናው የፌስቡክ ገጹ እና በኢንስታግራም ገጹ ላይ ባጋጠመው ችግር የአገልግሎት መቋረጥ አጋጥሞት እንደበረ አስታውቋል።

የፌስቡክ ኩባንያ ቃል አቀባይ እንዳስታወቁት፥ አሁንም ቢሆን የተወሰኑ ሰዎች ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን መጠቀም ላይ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ነገሮችን በአፋጣኝ ወደ ነበሩበት ለመመለስም የፌስቡክ ኩባንያ እየሰራ መሆኑን ነው ቃል አቀባዩ ያስታወቁት።

የድረ ገጾች መቋረጥን የሚከታተለው “ደወን ዳይሬክተር (DownDetector.com)” እንዳስታወቀው ከፌስቡክ መቋረጥ ጋር በተያያዘ በሺህዎች የሚቆሩ ችግሮች በበርካታ የዓለም ክፍል ከሚገኙ ተጠቃሚዎች መነሳታቸውን አስታውቋል።

ትናንት አመሻሽ ላይ ያጋጠመው የመቆራረጥ ችግሩ ሁሉንም ተጠቃሚዎች አላጋጠመም የተባለ ሲሆን፥ በርካቶች ላይ ደግሞ አንዳንድ የገጹ አገልግሎቶች ያለምስራት ችግር እና የፍጥነት መቀነስ እንደነበረም ታውቋል።

የፌስቡክ ገጻቸቸው ላይ ችግር እንዳጋጠማቸው ሪፖርት ካደረጉ ሰዎች ውስጥ 40 በመቶ ያክሉ ገጹ ሙሉ በሙሉ መቆሙን የገለጹ ሲሆን፥ 36 በመቶ ያክሉ ደግሞ ወደ ገጹ ለመግባት እና ለመውጣት መቸገራቸውን አስታውቀዋል።

ኢንስታግራም ገጽ ላይ ካጋጠሙ ችግሮች ውስጥ ደግሞ 25 በመቶ ያክሉ ወደ ገጹ ለመግባት መቸገራቸው የተገለፀ ሲሆን፥ 51 በመቶ ያክሉ ደግሞ ገጹ ላይ የሚመጣላቸውን መረጃዎች መመልከት አልቻሉም ነበር።

ምንጭ፦ www.huffingtonpost.co.uk