አፕል ታጣፊ አይፎን ስልኮችን በ2020 ለማምረት እየሰራ መሆኑ ተነገረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አፕል ታጣፊ አይፎን ስማርት ስልኮችን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 ለማምረት እየሰራ መሆኑ ታውቋል።

በአሁኑ ጊዜም አፕል ከኤል ጂ ኩባንያ ጋር በጥምረት ለመስራት እየተነጋገረ ላይ መሆኑም ተነግሯል።

አፕል እና የደቡብ ኮሪያው ኤል ጂ ኩባንያ እያደረጉት ያለው ውይይትም በኦ ሊድ ስክሪን ዙሪያ በጋራ ለመስራት መሆኑ ነው የተነገረው።

የደቡብ ኮሪያው ቤል የተባለ የዜና አውታር እንዳስታወቀው የአፕል ታጣፊ አይፎን ስማርት ስልኮች እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2020 ተመርተው ለገበያ የሚቀርቡ ይሆናል።

በቅርቡ ለገበያ የቀረበው አዲሱ የአፕል ምርት አይፎን X ስማርት ስልክ ከዚህ ቀደም ከነበሩ የአይፎን ስማርት ስልኮች በርካታ ለውጦች ተስተውለውበታል።

ይህም አፕል በቀጣይ ታጣፊ ስልኮችን ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ምልክቶችን ያሳያል ነው እየተባለ ያለው።

በርካታ የስማርት ስልክ አምራቾች ታጣፊ ስማርት ስልኮችን የመስራት ሀሳብ እንዳላቸው በመግለፅ ላይ ሲሆኑ፥ ሳምሰንግ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው።

የደቡብ ኮሪያው የቴክኖሎጂ ቁሶች አምራች ሳምሰንግ ታጣፊ ስልኮችን ዳግም ወደ ገበያው ለመመለስ እየሰራ መሆኑ ከተሰማም ዋል አደር ብሏል።

ሳምሰንግ አዲስ እየሰራ ነው የተባለው አዲሱ ታጣፊ አንድሮይድ ስማርት ስልክ “ጋላክሲ ፎልደር 2 / Galaxy Folder 2/” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፥ ኩዋል ኮም ፕሮሰሰር የሚጠቀም እና የባትሪ አቅሙ “2,000 mAh” ነው ተብሏል።

ታጣፊ አንድሮይድ ስማት ስልኩ 3.8 ኢንች ዲስፕሌይ ስክሪን፣ 8 ሜጋፒክስ የጀርባ ካሜራ እንዲሁም 5 ሜጋ ፒክስል የፊት ካሜራ የተገጠመለት ነው።

እንዲሁም 6.0.1 ማርሽማሎው አንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተም የሚጠቀመው ስማርት ስልኩ፤ 2 ጊጋ ባይት ራም እና 8 ጊባ ባይት ሊሰፋ የሚችል የመረጃ መያዣ አለው።

የሳምሰንግ ታጣፊ አንድሮይድ ስማርት ስልክ መቼ ገበያ ላይ ይውላል በሚለው ዙሪያ የተባለ ነገር የለም።

ምንጭ፦ www.cnet.com