ቻይና በሮቦት ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ፖሊስ ጣቢያ እየገነባች ነው

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በሮቦት ቴክኖሎጂ ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ ፖሊስ ጣቢያ እየገነባች መሆኑን ይፋ አድርጋለች።

ይህ የሰው ባለሙያ የማያስፈልገው ፖሊስ ጣቢያ በቻይና ከሚገኙ የግዛት ዋና ከተማዎች በአንዷ እንደሚከፈት ተጠቁሟል።

በተለይም ተገልጋዮችን ለመመዝገብ እና የአሽከርካሪ ምርመራ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማጣራት ይውላል ተብሏል ቴክኖሎጂው።

የፖሊስ ጣቢያው የአስተዳደር ስራ ሰዎችን የማያካትት መሆኑ በሳምንት የሰባት ቀናት እና 24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት አመቺ ያደርገዋልም ነው የተባለው።

በዚህም ሰዎች ለእረፍት እና ከስራ መልስ ወደ ቤት ሲሄዱ የሚባክነውን ጊዜ እንደሚያስቀር ታምኖበታል።

በቴንሴንት ኩባንያ የተሰራው ይህ ተክኖሎጂ የሰዎችን የፊት ገፅታ የሚያነብ ሲሆን፤ ፊታቸውን እንደመታወቂያ እንዲጠቀሙ ያደርጋል።

wuhan2.jpg

ይህ መሆኑ ደግሞ ሰዎች በጣቢያው ለሚያገኙት አገልግሎት የተለያዩ የማንነት መረጃዎችን በመሙላት የሚያባክኑትን ጊዜ እንደሚቆጥብ ተነግሯል።

ይህ በሮቦት የሚሰራ ፖሊስ ጣቢያ ሀሳብ በሌሎችም የመንግስት አስተዳደራዊ እና የአገልግሎት ተቋማት ቢተገበር መልካም ነው የሚል አስተያየትን አምጥቷል።

ቻይና በየጊዜው በዜጎች ህይወት ውስጥ ቴክኖሎጂ ፋይዳው የጎላ እንዲሆን የምታደርገው ጥረት ማሳያም ተደርጎ እየተወሰደ ነው።

 

 

ምንጭ፦ thenextweb.com