አፕል በአዲሱ የፈረንጆቹ አመት ሶስት አዳዲስ ስልኮችን ለገበያ ያቀርባል

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 5 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ግዙፉ የቴክኖሎጅ ኩባንያ አፕል በአዲሱ የፈረንጆቹ አመት በአዳዲስ ስልኮቹ ወደ ገበያ እንደሚመጣ እየተነገረ ነው።

የኩባንያውን አዳዲስ ስሪቶች የሚከታተሉት ባለሙያዎች እንዳሉት፥ ኩባንያው በ2018 ሶስት አዳዲስ ስልኮችን ይዞ ወደገበያ ይቀርባል።

አዳዲሶቹ ስልኮች በስክሪን ስፋታቸው ከእስካሁኖቹ ተለቅ ያሉና ቀለል ያለ ይዘት ያላቸው መሆኑም ተነግሯል።

ስልኮቹ በተለመደው ጠፍጣፋና ባለ ከርቭ ሆነው የተሰሩ ሲሆን፥ 5 ነጥብ 8፣ 6 ነጥብ 1 እና 6 ነጥብ 5 ኢንች የስክሪን ስፋት ያላቸው ናቸው።

ከዚህ ባለፈም ሁሉም ስልኮች ባለሙሉ ስክሪንና ተመጣጣኝ የሆነ የስክሪን ብርሃን ያላቸውና ለአጠቃቀም ምቹ ናቸው ተብሏል።

ባለ 5 ነጥብ 8 እና ባለ 6 ነጥብ 5 ኢንች ስልኮች ሙሉ ስክሪን ሆነው ከርቭ ያላቸው ሲሆን፥ ባለ 6 ነጥብ 1 ኢንች ስክሪን ስፋት ያለው ስልክ ደግሞ ጠፍጣፋ ነው።

ባለ 6 ነጥብ 5 ኢንች ስፋት ያለው ስልክ አይፎን ኤክስ ፕላስ ሲሆን፥ ባለ 6 ነጥብ 1 ኢንች ስፋቱ ደግሞ በአይፎን ኤክስ ሞዴል የሚቀርብ ይሆናልም ነው የተባለው።

6 ነጥብ 1 ኢንች ስፋት ያለው አይፎን ኤክስ ስልክ ከዚህ ቀደም ከቀረቡት የኩባንያው ምርቶች አንጻር ረከስ ባለ ዋጋ ለገበያ ይቀርባል ተብሏል።

ከአዳዲሶቹ የአፕል ስልኮች የተወሰኑ ይዘቶችና ከተገመተው ዋጋ ውጭ ግን ተጨማሪ ዝርዝር ነገር አልወጣም።

 

 


ምንጭ፦ www.cnbc.com