ቻይና በሱፐር ኮምፒውተሮች ብዛት ቀዳሚ ሆናለች

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 5 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በርካታ ቁጥር ያላቸው ግዙፍ ሱፐር ኮምፒውተሮች (የተለዩና ውስብስብ ስሌቶችን የሚሰሩ) ባለቤት ሆናለች።

በዘርፉ ላይ በተደረገ ጥናት የሩቅ ምስራቋ ሃገር የተለዩ የሂሳብ ስሌቶችን ያለ እንከን ይከውናሉ የሚባሉትን በርካታ ኮሚፒውተሮች በመያዝ ቀዳሚዋ መሆኗን ተረጋግጧል።

ግዙፎቹና ፈጣኖቹ ኮምፒውተሮች በሰከንድ ውስጥ በትሪሊየን የሚቆጠሩ ስሌቶችን የሚሰሩና ውስብስብ ነገሮችን የሚከውኑ እንከን አልባ መሆናቸው ይነገራል።

እስካሁንም ቻይና አለም ላይ ካሉት ፈጣን እና የተለዩ ኮምፒውተሮች ውስጥ 202 ሲኖራት፥ አሜሪካ ደግሞ 143 በመያዝ ትከተላለች።

አሜሪካ ከዚህ ቀደም እነዚህን ኮምፒውተሮች በብዛት በመያዝ ቀዳሚ የነበረች ቢሆንም፥ አሁን ላይ በቻይናውያን ተበልጣለች።

ጃፓን 35 በመያዝ ሶስተኛ ስትሆን አውሮፓዊቷ ጀርመን ደግሞ 20 ኮምፒውተሮችን በመስራት ተከታዩን ደረጃ ይዛለች።

ቻይናውናያን ለዘርፉ በሰጡት ልዩ ትኩረት አሁን ላይ ቀዳሚ ሲሆኑ፥ አለም ላይ ካለው ሱፐር ኮምፒውተር የ20 በመቶው ባለቤትና መገኛም ሆነዋል።

እነዚህ ኮምፒውተሮች በአብዛኛው ለየት ያለ ከባድና ውስብስብ ተግባርን ለመከወን ይረዳሉ።

ሃገራትም ለአየር ንብረት ለውጥ ጥናት፣ ለኒውክሌር ጦር መሳሪያ ልምምድ፣ ለአየር ትንበያና ሌሎችንም ውስብስብ ተግባራት ይከውኑባቸዋል።

ቻይና አሁን ላይ ባለፈው የፈረንጆች አመት በሰራችው “ታዩ ላይት” በተሰኘው ሱፐር ኮምፒውተሯ፥ በዘርፉ የፈጣን ሱፐር ኮምፒውተር ባለቤት ሆናለች።

ይህ ኮምፒውተር በሰከንድ 93 ትሪሊየን ስሌቶችን መስራትና ውስብስብ ነገሮችን መከወን የሚችል ስለመሆኑም ይነገራል።

ቻይናውያን ካላቸው ሱፐር ኮምፒውተር ብዛት በተጨማሪ፥ በያዙት ኮምፒውተር አማካይ የመስራት አቅምም ከአሜሪካውያኑ ልቀው ተገኝተዋል ነው የተባለው።

ጥናቱን ያደረጉት ባለሙያዎች ይህ የቻይናውያን የበላይነት በጠንካራ ስራ መምጣቱን ቢጠቅሱም፥ ሁሉም ሱፐር ኮምፒውተር ግን ለሃገራዊ ፍጆታ ብቻ የሚውል አለመሆኑን ይገልጻሉ።

አብዛኛዎቹ ኮምፒውተሮች በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሃገራት ለሚገኙ ኩባንያዎች የሚከራዩና ገንዘብ የሚያስገኙ ናቸው።

ቀሪዎቹ ደግሞ መከላከያውን ጨምሮ ሌሎች ውስብስብ ጉዳይ በሚታይባቸው ዘርፎች ለሃገራዊ ፍጆታ እንደሚውሉም ገልጸዋል።

 

 

 

ምንጭ፦ ቢቢሲ