ከታዳጊ ሴት ልጆች መካከል አንድ ሶስተኛ ያህሉ በቀጥታ ኢንተርኔት ፆታዊ ትንኮሳ ይደርስባቸዋል-ጥናት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ከታዳጊ ሴት ልጆች መካከል አንድ ሶስተኛ ያህሉ በተመሳሳይ እድሜ ላይ በሚገኙ ወንድ ልጆች በቀጥታ ኢንተርኔት ፆታዊ ትንኮሳ እንደሚደርስባቸው ቻይልድ ኔት የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት ያወጣው ጥናት አመላክቷል።

እድሜያቸው ከ13 እስክ 17 ዓመት ከሚሆናቸው ሴቶች መካከል 31 በመቶዎቹ ላልተፈለገ ወሲባዊ ትንኮሳ ግፊት ተደርጎባቸዋል።

በአንፃሩ በተመሳሳይ እድሜ የሚገኙ ወንድ ልጆች መካከል 11 በመቶ ያህሉ ተመሳሳይ ትንኮሳ ደርሶባቸዋል።

ለጥናቱ ቃለ መጠይቅ 1 ሺህ 559 ታዳጊዎች ቃለመጠይቅ ተደርጎላቸዋል።

በዚህም በአማካይ ከ10 ውስጥ አንዱ ጾታዊ ትንኮሳዎች በቀጥታ ኢንተርኔት ደርሶብናል ብለዋል።

26 በመቶ ታዳጊዎች በወሲባዊ ጉዳዮች ዙሪ በኢንተርኔት መነጋገሪያ መሆናቸውን አንስተዋል።

12 በመቶዎቹ ደግሞ ራቁት ገላቸውን በኢንተርኔት እንዲያጋሩ በጓደኞቻቸው ግፊት እንደተደረገባቸው ተናግረዋል።

ከሴት ልጆች መካከል 33 በመቶዎቹ ከወንዶች መካከል ደግሞ 14 በመቶዎቹ በኢንተርኔት በለጠፉት ምስል ላይ የሚሰጧቸው አስተያየቶች ፆታዊ ትንኮሳ ይዘት ያላቸው መሆናቸውን ነው የገለፁት።

ጥናቱ ፆታዊ ትንኮሳ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች እየተስፋፋ መሆኑን ገልጾ፥ ዋትስአፕ እና ስናፕቻትን እንደሚጨምር ጠቁሟል።

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በተለይም በትምህርት ቤቶች ታዳጊ ተማሪዎች በጓደኞቻቸው የቀጥታ ኢንተርኔት ፆታዊ ትንኮሳ እንዳይፈፀምባቸው የግንዛቤ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑንነው ያስታወቀው።

 

 

 

 

ምንጭ፦ቢቢሲ