የሁዋዌይ ቀጣይ ምርት "P11" ጥራቱ 40 ሜጋ ፒክስል የሆነ 3 የካሜራ ሌንስ ይኖረዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አሁን በገበያ ላይ እየዋሉ ያሉት ስማርት ስልኮች ከሚወዳደሩባቸው መስፈርቶች ውስጥ የካሜራቸው ጥራት አንዱ ነው።

በርካታ የስማርት ስልክ አምራቾችም ጥራት ያለው ምስል ለማንሳት ያስችል ዘንድ በአንድ ስልክ ጀርባ ላይ ሁለት ሌንሶችን እስከመግጠም ደርሰዋል።

የቻይና የስማርት ስልክ አምራቹ የሁዋዌይ ደግሞ ቀጣይ የሚያመርተው ስማርት ስልክ የተሻለ የካሜራ ጥራት እንዲኖረው እየሰራ መሆኑ ተነግሯል።

የሁዋዌይ ቀጣይ ምርት የሆነው "P11" ስማርት ስልክ ካሜራ ምስል የማንሳት ጥራቱ 40 ሜጋ ፒክስል እንደሚሆን ተነግሯል።

ከዚህ በተጨማሪም "P11" ስማርት ስልክ ምስል የማንሳት አቅማቸው ከፍተኛ የሆነ ሶስት የካሜራ ሌንስ በጀርባው በኩል ብቻ እንደሚገጠምለት ሪፖርቶች አመልክተዋል።

የ"P11" ስማርት ስልክ የፊት ለፊት ካሜራ ጥራትም 24 ሜጋ ፒክስ መሆኑ መረጃዎች አመልክተዋል።

አዲሱ "P11" ስማርት ስልክ፥ እስከ 5 ነጥብ 8 ኢንች የስክሪን ስፋት ሊኖረው ይችላል የተባለ ሲሆን፥ የራም አቅሙ 6 ጊጋ ባይት እንደሚሆን ተገምቷል።

እንዲሁም በሁለት አይነት የመረጃ መያዣ ቋት (ስቶሬጅ) ለገበያ ሊቀርብ ይችላል፤ እነዚህም 64 ጊጋ ባይት እና 128 ጊጋ ባይት ነው ተብሏል።

የባትሪው አቅምም "3200mAh" እንደሚሆን ነው የተገለፀው።

ቀጣይ የሁዋዌይ ምርት የሆነውን "P11" ዝርዝር ይዞ የወጣው ኢቫን ብላስ የተባለ የትዊተር ገፅ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም መረጃዎችን አሾልኮ በማውጣት ይታወቃል።

ስማርት ስልኮቹ መቼ ለገበያ ይቀርባሉ የሚለው ላይ ግን እስካሁን ምንም ያልታወቀ ሲሆን፥ በቀጣዩ የአውሮፓውያኑ 2018 ለገበያ ሊቀርብ እንደሚችል ተገምቷል።

የቻይና የስማርት ስልክ አምራቹ የሁዋዌይ "P10" የተባለውን ስማርት ስልኩን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየካቲት ወር 2017 ለገበያ ማቅረቡ ይተወሳል።

ምንጭ፦ indianexpress.com