ተመድ ፌስ ቡክ በማይናማር የጥላቻ ንግግሮች እንዲዛመቱ ረድቷል በሚል ወቀሰ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሙያተኞች በማይናማር እየደረሰ ካለው ሰብዓዊ ቀውስ ጋር በተያያዘ ፌስ ቡክ ላይ ወቀሳ ሰንዝረዋል።

የኮሚሽኑ የባለሙያዎች ቡድን ግዙፉ የማህበራዊ ትስስር ገጽ፥ በሃገሪቱ ከተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ጋር በተያያዘ የጥላቻ ንግግሮች እንዲሰራጩ የራሱን ሚና ተጫውቷል በሚል ወቀሳ አቅርበዋል።

የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሊቀመንበር፥ በማይናማር የሮሂንጊያ ሙስሊሞች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሳይፈጸም አልቀረም በሚል የሃገሪቱን መንግስት ወቅሰዋል።

በማይናማር የመንግስታቱ ድርጅት እውነታ አፈላላጊ ኮሚቴ ሊቀመንበር ማርዙኪ ዳሩስማን ደግሞ፥ በማይናማር እየተፈጸመ ላለው ሰብዓዊ ቀውስ ማህበራዊ ትስስር ገጾች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ሊቀመንበሩ እንደ ፌስ ቡክ ያሉ ማህበራዊ ትስስር ገጾች፥ የሚሰራጩ መረጃዎችን ከፍ ወዳሉና ግጭት ቀስቃሽ ወደ ሆኑ አዝማሚያዎች በመውሰድ በኩል ከፍ ያለ ሚና ይጫወታሉም ነው ያሉት።

በማይናማር ካለው ሁኔታ ጋር በተያያዘም በማህበራዊ ትስስር ገጽ የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች በከፍተኛ ደረጃ ተዛምተዋል ብለዋል።

ፌስቡክም የሚወጡ መረጃዎችና የጥላቻ ንግግሮችን በማዛመት በሃገሪቱ ቀውስ የራሱን ሚና ማበርከቱንም አንስተዋል።

የማይናማር መንግስት ፌስ ቡክን መረጃ ለህዝብ ለማድረስና ለማሰራጨት እንደተጠቀመበት የሚናገሩት ደግሞ፥ በመንግስታቱ ድርጅት የማይናማር ጉዳይ አጣሪ ቡድንን የሚመሩት ያንጊ ሊ ናቸው።

ገጹ በዚያች ሃገር ለሆነው ሁሉ አስተዋጽኦ አለው የሚሉት ወይዘሮ ሊ፥ በሃገሪቱ የጥላቻ ንግግሮች በከፍተኛ ደረጃ እንዲዛመቱ ረድቷልም ነው የሚሉት።

ከዚህ አንጻርም ጽንፈኛ የማይናማር ቡድሃ እምነት ተከታዮች በራሳቸው የፌስ ቡክ ገጽ አማካኝነት በሮሂንጊያ ሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ንግግርን ለማሰራጨት ገጹን መጠቀማቸውንም ያነሳሉ።

አሁን ላይም ፌስ ቡክ ሲመሰረት ከነበረው አላማ የተለየ ገጽታን እየተላበሰና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እያመራ ነው ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

የኮሚሽኑ አጣሪ ባለሙያዎችም የፌስ ቡክ ገጽ በማይናማር ላልተፈለገና በጎ ላልሆነ አላማ መዋሉን በመጥቀስ፥ ለተፈጠረው ቀውስም ሆነ በሮሂንጊያ ሙስሊሞች ላይ ለደረሰው ሰብዓዊ ቀውስ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

የፌስ ቡክ ኩባንያ በጉዳዩ ላይ ቀጥተኛ መልስ ባይሰጥም፥ በማይናማር ካለው ሁኔታ ጋር ተያይዞ ግን የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን ገልጿል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ በሃገሪቱ ስመ ጥር የሆኑ የቡድሃ ሰባኪዎችን የፌስ ቡክ አካውንት ለተወሰነ ጊዜ እስከማገድ የደረሰ እርምጃ መውሰዱንም ነው የገለጸው።

ይሁን እንጅ ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንጻር አሁንም በርካታ የማጣራት ስራዎችን እየሰራሁ ነው ብሏል።

የጥላቻና አመጽ ቀስቃሽ ንግግሮችን በማስወገድ ጉዳዩን እልባት ለመስጠት እየሰራ መሆኑንም ጠቅሷል።

በማይናማር ራክሂን ግዛት የሚገኙ የሮሂንጊያ ሙስሊሞች እየደረሰባቸው ባለው ሰብዓዊ ቀውስ ሳቢያ ከ650 ሺህ በላይ የሚሆኑት፥ ወደ ባንግላዴሽ መሰደዳቸው ይነገራል።

የተመድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አጣሪ ቡድን ደግሞ የሃገሪቱ መንግስት በሮሂንጊያ ሙስሊሞች ላይ ከፍ ያለ በደል ፈጽሟል በሚል ጉዳዩን እየመረመረ ይገኛል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የሃገሪቱ ከፍተኛ የጸጥታና ደህንነት ሃላፊዎች፥ ተፈጽሟል ስለተባለው ጉዳይ በቂ ማስረጃ እንዲያቀርቡለትም ጠይቋል።

 

 


ምንጭ፦ ሬውተርስ