ጤነኛ ኑሮ


አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰው ልጅ ጤናውን የመጠበቅ ግላዊ ሃላፊነት ቢኖርበትም በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ትኩረት ባለመስጠት ለጉዳት ሊዳረግ ይችላል፡፡

በየቀኑ መመገብ ስለሚገባን ምግብ፣ መውሰድ ስላለብን የውሃ መጠን እና እረፍት እንዲሁም መስራት ስለሚገባን አካላዊ እንቅስቃሴ ስንቶቻችን ተጨንቀን ወይም በሚመከረው ልክ ተግብረን እናውቃለን?

የሆነው ሆኖ ሰዎች በዕለት ከዕለት የኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ ከጤናቸው ጋር በተያያዘ ሊሰሯቸው የሚችሉ የጤና ስህተቶችን ከዚህ በታች አቅርበናል።

1. የምግብ ምርጫ እና የሚሰሩት አካላዊ እንቅስቃሴ አለመጣጣም

ሰዎች ከተወሰነ ጊዜ በፊት የተመገቡትን ምግብ ከመጠን በላይ የካሎሪ ክምችት እንዳይኖረው በሚል በአካላዊ እንቅስቃሴ ተቃጥሎ እንዲጠፋ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡

ሆኖም የስነ ምግብ እና አካላዊ እንቅስቃሴ ባለሙያዎች በየዕለቱ መመገብ ያለብንን ምግብ እና የምንሰራውን አካላዊ እንቅስቃሴ ማጣጣም እንዳለብን ይናገራሉ።

በተለይም ብዙ የሰውነት እንቅስቃሴ ካደረግን በኋላ የተቃጠለውን የሰውነታቸውን ሃይል የሚተካ ጥሩ ምግብ ልንመገብ ይገባል ነው የሚሉት፡፡

እንዲሁም የአመጋገብ ስርዓታችን እና የምግብ አመራረጣችን ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡

በቀን ውስጥ አትክልት እና ፍራፍሬ መመገብንም መክረዋል፡፡

2. ጉበትን እንደ ዋና የሰውነት ክፍል አለመመልከት

ስለ ሰው ልጅ አጠቃላይ ጤንነት ሲታሰብ የጉበት ሚና ከፍተኛ ነው፡፡

ሆኖም ሰዎች በየቀኑ ጉበት ማጠራቀም የሌለበትን ንጥረ ነገር ሳይመርጡ በሚመገቡት እና በሚጠጡት ነገር ጉዳት ያደርሱበታል፡፡

ጉበት ብዙ ንጥረነገር ከታጨቀበት ደግሞ ሰውነታችን የሚያገኘውን በቂ ሃይል እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡

የእንቅልፍ እጥረት፣ የሆርሞን አለመመጣጠን እና ሌሎችም የጤና ቀውሶች ይከሰታሉ፡፡

በመሆኑም በየዕለቱ ጉበታችን ሊይዘው የሚችል በቂ ንጥረ ነገርን በምግቦቻችን እና በምንጠጣቸው ነገሮች መጥነን መጠቀም ተገቢ ነው፡፡

በተለይም እንደ አልኮል፣ ቡና እና ስኳር ያለባቸው ሌሎች አነቃቂ ነገሮችን አወሳሰድ መመጠን ጥቅሙ ላቅ ያለ ነው፡፡

3. ሰውነታችን ለሚያሳየን ምልክት ትኩረት መንፈግ

የሰውነት ክፍላቸው ላይ ለሚፈጠሩ ጥሩ ያልሆኑ ስሜቶች ትኩረት የማይሰጡ ሰዎች ለከፋ የጤና ችግር ይዳረጋሉ፡፡

በተለይም የህመም ስሜቶቹ ሁልጊዜም የሚከሰቱ እና ለውጥ ብዙ የማያሳዩ ከሆነ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ትኩረት አይሰጧቸውም፡፡

ለአብነትም የራስ ህመም፣ ሆድ መንፋት እና ድርቀት ከሚዘወተሩ የህመም ምልክቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፥ በትኩረት የሚከታተሏቸው ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡

የጤና ባለሙያዎች ግን እንዲህ አይነቱ ትኩረት የለሽነት በመጨረሻ ዋጋ ያስከፍላል ይላሉ፡፡

ስለሆነም ከላይ የቀረቡት ዓይነት የህመም ስሜቶች ሲከሰቱ አመጋገብን ማስተካከል፣ ዕረፍት ማድረግ እና አካላዊ እንቅስቃሴ መስራት እንደሚገባ ተመክሯል፡፡

በየእለቱ ለሚያጋጥሙ የህመም ስሜቶች ትኩረት መስጠት እና የሚገባውን መፍትሔ መተግበር ግዴታ ነው ተብሏል፡፡

4. አዕምሮን እና ሰውነትን አረፍት እንዲወስድ አለማድረግ

ብዙ ጊዜ በተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስራዎች ተወጥረው የሚውሉ ሰዎች፥ ለሰውነታቸው እና ለአዕምሯቸው እረፍት ላይሰጡ ይችላሉ፡፡

አንዳንዶቹ ከስራ መልስ ስማርት ስልክ፣ ኮምፒውተር ወይም ቴሌቪዥን ላይ በማፍጠጥ አዕምሯቸው እረፍት እንዳያገኝ ሊያደርጉ እንደሚችሉም ነው የተጠቆመው፡፡

ይህ ደግሞ የሰዎች አዕምሮ እና ሰውነት በየቀኑ እና በየሳምንቱ ማግኘት የሚገባውን እረፍት ባለማግኘቱ ለጤና ቀውስ ይዳርጋል፡፡

በመሆኑም ስራን እና እረፍትን በእቅድ በማድረግ የተወሰነ ሰዓት እረፍት የተወሰነ ሰዓት ደግሞ ስራ ላይ ማተኮር ለጤና መልካም ነው፡፡

 

 

 

 

 

ምንጭ፦ www.huffingtonpost.co.uk

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2009 ኤፍ.ቢ.ሲ) የጨጓራ ካንሰር በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያጠቃል፡፡

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፅዱ ባልሆነች ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው፤ የትኛውም አካባቢ ብንሄድ እንኳ ከተለያዩ ተህዋሲያን የፀዳ ቦታን ማግኘት አዳጋች ነው።

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በደቡባዊ ጣሊያን የምትገኘው የፒዮፒ መንደር “የአለማችን ጤናማ መንደር” የሚል ስያሜን ካገኘች ሰነባብታለች።

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ራስን ከሌሎች ጋር ማወዳደርና ማነጻጸር የተለመደና በስፋት የሚስተዋል ጉዳይ ነው።