ዛፍ መሳይ እጅ ያለው ባንግላዲሻዊ ተፈጥሯዊ እጁን አግኝቷል

አዲስ አበባ፣ ጥር 2፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አቡል ባጃንዳር “ዛፍ መሳይ እጅ ያለው” በመባል ዓለምን ያነጋገረ የ27 ዓመት የባንግላዲሽ ዜጋ ነው፡፡

በሀገሪቱ አንዲት ትንሽ ከተማ የሚኖረው ባጃንዳር፥ በዓለም ላይ አልፎ አልፎ ብቻ ከቆዳ ጋር ግንኙነት ባለው ኪንታሮት አምጪ ቫይረስ ባጋጠመው በሽታ ከ10 ዓመቱ ጀምሮ ሲሰቃይ ቆይቷል።

እጁ ላይ ባጋጠመው በሽታም የሁለት እጆቹ ጣቶች የዛፍ ቅርፅ ባለው አዳጊ ኪንታሮት ተጠቅተዋል፡፡ 

tree_man_1.jpg

ይህ ዛፍ መሳይ ኪንታሮትም በዓመታት ውስጥ እድገቱ እየጨመረ ሲመጣ በ2016 የካቲት ወር ተፈጥሯዊ እጁን ሊያስገኝለት የሚችል ቀዶ ህክምና ማድረግ ይጀምራል።

ህክምናው ከተጀመረ ወዲህ እጁን ለማግኘት 16 የህክምና ሂደቶችን ያለፈ ሲሆን ከሆስፒታል ከመውጣቱ በፊትም ቀሪ ህክምናዎችን መከታተል እንዳለበት ተነግሮታል፡፡

treeman_3.jpg

በዳሃካ የህክምና ኮሌጅ ሆስፒታል ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ሃኪም የሆኑት ዶክተር ሰማናት ላል ሴን ለሲ ኤን ኤን በሰጡት ቃለመጠይቅ "ባጃንዳር የህመሙ ምልክት የታየበት ከ10 ዓመቱ ጀምሮ ነው፤ የኪንታሮቱ እድገትም እጁን ዛፍ ያስመሰለው ሲሆን ስቃዩንም አብዝቶበታል፤ ህይወቱን የነጠቀው ያህል እንዲሰማውም ነው ያደረገው፤ ይህን ተከትሎም ዓለም ሁሉ መነጋገሪያው አድርጎታል" ነው ያሉት፡፡

ባጃንዳር ቀዶ ህክምና ሳይደረግለት በፊት መብላት፣ መጠጣት፣ መጻፍ፣ ጥርሱን ማፅዳትም ሆነ ራሱን ችሎ ሰውነቱን መታጠብ አይችልም ነበር፤ አሁን የተደረገለት ህክምና ግን እነዚህን ማድረግ ያስችለዋል ነው ያሉት ዶክተር ላል ሴን፡፡ 

treeman_gained_his_hand.jpg

"እንደማንኛውም ሰው ጥሩ ኑሮን መኖር እፈልጋለሁ፤ ልጄን ማቀፍ እና በእጆቼ መዳሰስ እፈልጋለሁ" ያለው ባለትዳር እና የአንድ ሴት ልጅ አባት ባጃንዳር ምስጋና ለቀዶ ጥገና ባለሙያዎቹ ፍላጎቱ ተሳክቶለታል።

ዶክተር ላል ሴን እንደተናገሩት ባጃንዳር አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን የእጁ ቅርጽም ተመልሶለታል።

“በእጁ መጉረስ እና መጻፍም ችሏል፤ ከዚህ በኋላ የሚቀረው የህክምና ሂደት ቢኖር የእጁን ውበት መመለስ ብቻ ነው” ብለዋል ዶክተር ላል ሴን።

 

ምንጭ፦ ሲ ኤን ኤን

 

 

በምህረት አንዱዓለም

 

android_ads__.jpg