በእረፍት ቀናት የሚሰሩ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ለጤናችን ጠቃሚ ናቸው

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አንድ ሰው ጤንነቱን ለመጠበቅ ቢያንስ በሳምንት ለሶስት ቀናት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት አንዳለበት ይመከራል።
ሆኖም ግን ሳምንቱን በሙሉ በስራ በመጨናነቃችን የተነሳ የአካል ብቃት መስሪያ ጊዜ ስናጣ ይስተዋላል።

ይህ ችግር የለውም የሚሉን ተመራማሪዎች በሳምንት ውስጥ ባሉት የእረፍት ቀናችን ማለተም ቅዳሜ እና እሁድ ላይ ብቻ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት ለጤንነታችን አይነተኛ ፋይዳ አለው ይላሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ያስቀመጠው መስፈርት እንደሚያመለክተው፥ አንድ ሰው ጤናማ የሆነ ኑሮን ለመምራት በሳምንት ወስጥ ለ150 ደቂቃዎች የአካል ብቃት እንቅስቃሴን መስራት ይጠበቅበታል።

ሆኖም ግን ይላሉ ተመራማሪዎች ይህንን ሁሉ መስራት የማይችሉ ሰዎች የእረፍት ቀናቸው በሆኑት ቅዳሜ እና እሁድ ላይ ብቻ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ቢሰሩ ያለጊዜ የሚከሰት ሞትን በሶስት እጥፍ መቀነስ ይችላሉ ብለዋል።

ጥናቱ እድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ በሆኑ ከእንግሊዝ እና ስኮትላንድ የተወጣጡ 64 ሺህ ሰዎች ላይ ነው የተካሄደው።

ከላፍብራፍ ዩኒቨርሲቲ እና ሲድኒ ዩኒቨርሲቲ የተወጣጡ ተመራማሪዎች በጥናቱ ላይ የተሳተፉትን ሰዎች ዳታ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በሚሰሩበት ጊዜ ጤንነታቸው ምን ይመስላል የሚለውን ለ18 ዓመታት ሲያጠኑ ቆይተዋል።

በጥናታቸውም ሰዎች በሳምንት ውስጥ ለብዙ ቀናት ወይም ለጥቂት ቀናት እንዲሁም ለረጅምም ይሁን ለአጭር ሰዓት የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ቢሰሩ፥ የሚያገኙት የጤና ጠቀሜታ ግን ተቀራራቢ ነው።

ይህ በጣም የተጨናነቀ ሰዓት ላላቸው እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በሳምንት ውስጥ ባሉ የእረፍት ቀናት ብቻ ለመስራት ለሚገደዱ ሰዎች መልካም ዜና መሆኑም ተነግሯል።

በሳምንት ወስጥ ካሉ የእረፍት ቀናት ወስጥ በአንዱ ወይም በሁለቱ ቀናት የአካል እንቅስቃሴን የሚሰሩ ሰዎች ከልብ ጋር በተያያዘ በሚከሰት የጤና እክል የመሞት እድላቸው በ41 በመቶ የቀነሰ ሲሆን፥ በካንሰር የመሞት እድላቸውም በ18 በመቶ የቀነሰ መሆኑ በጥናቱ ተብራርቷል።

በሳምንት ሶስት ቀን ወይም በየእለቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የሚሰሩ ሰዎች ደግሞ ከልብ ጋር በተያያዘ የጤና እክል የመሞት እድላቸው በ41 በመቶ እንዲሁም በካንሰር የመሞት እድላቸውም በ21 በመቶ የቀነሰ ነው።

በሳምንት ውስጥ በጣም ዝቅትኛ የተባለ ወይም በቂ ነው በማይባል ደረጃ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የሚሰሩ ደግሞ ከልብ ጋር በተያያዘ የመሞት እድላቸው በ37 በመቶ እንዲሁም በካንሰር የመሞት እድላቸውም በ14 በመቶ የቀነሰ ነው ተብሏል።

የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ ለአላማ የሚሰራ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለጤንነታችን ቁልፍ የሆነ መሳሪያ ነው

ምንጭ፦ ቢቢሲ

android_ads__.jpg