ለጤናማ አዕምሮ ቁርስዎን እንቁላል ቢያዘወትሩ መልካም ነው ተብሏል

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አዘውትሮ ቁርስ እንቁላል መመገብ ለአዕምሮ ህመም የመጋለጥ እድልን ከፍ እንደማያደርግ አንድ ጥናት አመለከተ።

እንቁላልን መመገብ የአዕምሮ ብቃትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ይታወቃል።

ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች እንቁላል አዘውትሮ መመገብ ለልብ ህመም፣ ከፍተኛ የደም ግፊት እና ለክብደት መጨመር እንደሚዳርግ ጠቁመዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የልብ፣ የደም ቧንቧዎች ጉዳት እና የደም ዝውውር መዛባት ለከፍተኛ የመርሳት በሽታ ያጋልጣል የሚለው መረጃም ተደጋግሞ ተነስቷል።

አዲሱ ጥናት ግን እንቁላል መመገብ በደም ውስጥ በሚገኝ የኮሊስትሮል መጠን ላይ መጠነኛ ተፅዕኖ ነው የሚኖረው ብሏል።

የፊንላንድ ተመራማሪዎች እድሜያቸው በ42 እና 60 የሚገኝ የማስታወስ ችግር ያለባቸውን 2 ሺህ 497 ወንዶችን አመጋገብ አጥንተዋል።

ከጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል 337 የሚሆኑት ባለፉት 22 አመታት ውስጥ በከፍተኛ የመርሳት በሽታ ተጠቅተው ተገኝተዋል።

በአሜሪካ ኪሊኒካል ኑትሪሽን ጆርናል ላይ በወጣት የጥናት ውጤት ከእነዚህ ውስጥ ሲሶ የሚሆኑት አፖሊፖፕሮቲን ኢ (APOE4) የተሰኘ ጂን እንዳላቸው ተረጋግጧል።

አፖሊፖፕሮቲን ኢ ለደም ዝውውር እና የአዕምሮ መቃወስ ችግር ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ይታወቃል።

ምንም እንኳን APOE4 ጂን ያላቸው ሰዎች ለበሽታዎቹ የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ቢሆንም በዘር ያገኙት ይሁን እንቁላል በመመገባቸው ያዳበሩት ምንም ማረጋገጫ የለም ብለዋል ተመራማሪዎቹ።

በምስራቅ ፊንላድ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩት እና የጥናቱ ፀሃፊ ፕሮፌሰር ጀርኪ ቪርታነን፥ ኮሌስትሮልም ይሁን እንቁላል መመገብ ከአዕምሮ መቃወስ አልያም ከከፍተኛ የመርሳት በሽታ ጋር ግንኙነት የላቸውም ብለዋል።

እንቁላል መመገብ የአዕምሮን ብቃት ማሳደጉን አረጋግጠናል ያሉት ፕሮፌሰር ጀርኪ፥ ፈተናዎችን የመስራት ብቃትን እንደሚጨምር ተናግረዋል።

ጥናቱ ከፍተኛ ኮሌስትሮል ያላቸው ምግቦችም ሆነ እንቁላልን አዘውትሮ መመገብ የማስታወስ ችሎታ ችግርን አያመጡም ብሏል።

ባለፈው የፈረንጆቹ አመት 2016 የተደረገ ጥናትም በቀን ውስጥ አንድ እንቁላል መመገብ በስትሮክ የመጠቃት እድልን በ12 በመቶ እንደሚቀንስ ማመላከቱ የሚታወስ ነው።

የአሜሪካ ተመራማሪዎችም እንቁላልን መመገብ ከልብ ህመም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑን ማስታወቃቸው አይዘነጋም።

 

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk/

 

 

በፋሲካው ታደሰ

 

android_ads__.jpg