ከስኳር በሽታ በ4 ወራት ውስጥ ለማገገም የሚረዱ የህክምና ዘዴዎች መገኘታቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 8 ፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ተመራማሪዎች ሁለተኛው አይነት (ታይፕ 2) ከሚባለው የስኳር በሽታ ታማሚዎች በአራት ወራት ከህመማቸው እንዲያገግሙ የሚያስችሉ ህክምናዎችን ማግኘታቸውን ተመራማሪዎች ተናግረዋል።

በሽታውን የአካል ብቃትን እንቅስቃሴ በማድረግ፣ ካሎሪን በመመጠን እና እንክብሎችን በመውሰድ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚቻል ነው ጥናቱ ያመላከተው፡፡

ሁለተኛው አይነት (ታይፕ 2) ስኳር በሽታ በብሪታኒያ 4 ሚሊየን ሰዎችን የሚያሰቃይ በሽታ ሲሆን፥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው፡፡

ሆኖም ተመራማሪዎች ከስኳር ምጣኔ እስከ በሽታ ፈፅሞ ማከም የደረሰ የህክምና ውጤት አግኝተንለታል እያሉ ነው፡፡

ለአራት ወራት በተደረገው ጥናት ላይ ከተሳተፉተ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት ምርመራ ሲደረገላቸው ምንም ዓይነት የሰኳር በሽታ ምልክት አልተገኘባቸውም፡፡

የጥናቱ መሪ የሆኑት የማክማስተር ዩኒቨርሲቲው ተመራማሪ ናታሊ ማክልኔስ፥ ግኝቱ የታይፕ 2 የስኳር ህመም ለክብደት ቅነሳ ከሚደረግ ቀዶ ህክምና በሻገር በቀላል የህክምና መንገዶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ይድናል፡፡

ታይፕ 2 የስኳር ህመም የሚከሰተው በሰውነታችን ውስጥ ስኳርን የሚመጥነው ኢንሱሊን ከሌለ ወይም ደግሞ ኢንሱሊን ስራውን በአግባቡ ሳይሰራ ሲቀር ነው።

ይህ ሲሆን ግሉኮስ በደም ውስጥ መሰራጨቱ ይቆማል፤ በዚህ ጊዜ ደግሞ በደም ውስጥ ያለው የሰኳር መጠን ይጨምራል፤ ይህም የደም ህዋሳት እንዲዳከሙ ያደርጋል፡፡

በጥናቱ 83 ተሳታፊዎች በሶስት ቡድን ተከፍለው ተሳትፈዋል፡፡

ሁለቱ ቡድኖች ግለሰባዊ የአካል እንቅስቃሴዎችን እንዲደርጉ እና በቀን ውስጥ የሚወስዱትን የካሎሪ መጠን ቀንሰው ከ500 እስከ 700 ካሎሪ እንዲመገቡ ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም እንክብሎችን እንዲወስዱ ተደርገዋል፡፡

ይህን የህክምና ሙከራ የመጀመሪያዎቹ ቡድኖች ለ8 ሳምንታት ሲሞከርባቸው፥ ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ለ16 ሳምንታት ተከታትለዋል፡፡

ሶስተኛው ቡድን ደግሞ ለጥናቱ ሚዛናዊነት እና ለውጡን ለመመዝገብ መደበኛ የሆነ ክትትል ተደርጎላቸዋል፡፡

ከሶስት ወራት የህክምና ሙከራ በኋላም 16 ሳምንታት ክትትል ከተደረገባቸው 27 ተሳታፊዎች ውስጥ 11 የሚሆኑት በሙሉ እና በከፊል ከበሽታው አገግመዋል፡፡

ስምንት ሳምንታት የህክምና ሙከራውን ካደረጉት 28 ሰዎች ውስጥ ደግሞ ስድስቱ አገግመዋል፡፡

የጥናቱ መሪ እንዳሉት ሁሉም የስኳር ታማሚዎች ጥሩ ህይወት እንዲኖራቸው እና በሰውነታቸው ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን ለማመጣጠን ያለመ ነው፡፡

እንዲሁም ጣፊያ እረፍት እንዲያገኝ፣ የስብ መጠንን እንዲቀንስ ያደርጋል ነው ያሉት፡፡

የህክምና ሙከራው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ሰፋ ያለ ጥናት ለማድረግ አቅዷል የጥናት ቡድኑ፡፡

ምንጭ፡-www.huffingtonpost.co.uk