አቮካዶ ከልብ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመከላከል…

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 13፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አቮካዶን መመገብ ከልብ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ለመከላከል እንደሚረዳ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል።

ተመራማሪዎቹ ከዚህ ቀደም አቮካዶ መመገብ ምን አይነት ጥቅም ያስገኛል በሚለው ዙሪያ የተረሱ 100 ጥናቶች ላይ ባደረጉት ምልከታ እና ትንተና ነው ይህን ያሉት።

በዚህም የአቮካዶ ውሰጠኛውን ክፍል፣ የአቮካዶ ዘይት እና ልጣጩ የልባችንን ጤንነት ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ሚና እንዳለው መለየታቸውን አስታውቀዋል።

አቮካዶ ውስጥ የሚገኙ ተፈጥሯዊ ንጥረ ነገሮች ጎጂ የሆነ የኮሌስትሮል መጠንን እና ለክፈተኛ የደም ግፊት የመጋለጥ እንድልን በመቀነስ እንዲሁም ከመጠን ያለፈ የሰውነት ውፍረት እንዳይከሰትብን በማድረግ ልባችን ጤነኛ እንዲሆን ያደርጋል ነው የተባለው።

በአቮካዶ የበለፀገ የአመጋገብ ስርዓት ሰውነታችን ጥሩ የሆነ የኮሌስትሮል መጠን እንዲኖረው ይረዳናል የሚሉት በተመራማሪዎቹ፥ ይህም መጥፎ የሆነ የኮሌስትሮል መጠንን በመቀነስ እንደሆነ ነው የሚያብራሩት።

ይህም በጣም ወሳኝ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ መጥፎ የሆነ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን ለልብ ህመም የመጋለጥ ምልክት በመሆኑ ነው ብለዋል።

ተመራማሪዎች በጥናቶቹ ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ አቮካዶ ለከፍተኛ የደም ግፊት ተጋላጭነትን ይቀንሳል ያሉ ሲሆን፥ ከመጠን ላለፈ የሰውነት ውፍረት እና ለ ሁለተኛው አይነት (ታይፕ 2) የስኳር በሽታ እንዳንጋለጥም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

ከዚህ ቀደም የተሰሩ አብዛኛ ጥናቶች በብዛት የአቮካዶ የውስጠኛውን ክፍል መመገብ ላይ ብቻ ያተኮሩ ሲሆን፥ ሆኖም ግን አንዳንድ ጥናቶች የአቮካዶ ልጣጭ፣ ዘር እና ዘይት ለጤና ያላቸውን ጠቀሜታ ዘርዝረዋል።

እንደ ተመራማሪዎቹ ገለጻ ግን ከዚህ በፊት እንደምንመገበት ጣፋጩን የአቮካዶ ክፍል ብቻ ብንመገብ የሚያስገኝልን የጤና ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው።

የልብ ህመም በዓለማችን ላይ ለሚከሰት ሞት በምክንያትነት ከሚቀመጡት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዝ ሲሆን፥ በአሜሪካ ብቻ በየዓመቱ 600 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከልብ ጋር በተያያ የጤና ችግር ህይወታቸውን ያጣሉ።

ታዲያ በየእለቱ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን መስራት፣ እንደ ሲጋራ ማጨስ ያሉ መጥፎ ልማዶችን ማስወገድ፣ የደም ግፊታችንን መከታተል እና በየጊዜው ወደ ጤኗ ተቋም በመሄድ የህክምና ክትትል በማድረግ የልብ ህመም ተጋላጭነታችንን መቀነስ እንችላለን።

እንዲሁም እንደ እንደ አቮካዶ ያሉ ለልብ ጤንነትጠቃሚ የሆኑ ምግቦችን በምግባችን ውስጥ በማካተት የአመጋገብ ስርዓታችንን ማስተካከልም የልብ ህመም ተጋላጭነታችን ለመቀነስ ይረዳል ነው የተባለው።

ምንጭ፦ www.huffingtonpost.com