እንቁላል የስኳር በሽታና የመርሳት ችግርን ጨምሮ በርካታ የጤና እክሎችን ለመከላከል መታዘዝ አለበት- ጥናት

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች ያሉት እንቁላል፤ ከስኳር በሽታ አንስቶ እስከ የጡንቻ መዛል፣ የመርሳት ችግር እና በርካታ የጤና እክል ላለባቸው ሰዎች መታዘዝ እንዳለበት አዲስ ጥናት አመልክቷል።

እንቁላል በውስጡ የያዘው የፕሮቲን፣ የቫይታሚን እና የተለያዩ ንጥረ ነገሮች ውህድ ተመራጭ አድርጎታል የተባለ ሲሆን፥ ስለዚህም እንቁላልን እንደ “ተፈጥሯዊ ባለብዙ ቫይታሚን” ለህመምተኞች መታዘዝ ይችላል የሚለው በጥናቱ ተብራርቷል።

በስኮትላንድ የሚገኝ የስነ ምግብ ምርምር ማእከል ነው የጥናት ውጤቱን ያወጣው።

ጥናቱ በእንቁላል ውስጥ ያሉትን ከፍተኛ ጥራት ያለው ፕሮቲን እና ፋቲ አሲድ በተጨማሪ በበርካታ ምግቦች ውስጥ የማይገኙትን እንደ ቫይታሚን ቢ እና ዲ፣ ሲሊየም፣ አዮዲን እና ክሎሪን ያሉ ከፍተኛ ንጥረ ነገሮችን በውስጡ እንደያዘ ተመልክቷል።

አዲስ የተገኘው ጥናትም ከዚህ ቀደም በስህተት እንቁላል በውስጡ ከፍተኛ የኮሌስትሮል መጠን ስላለው ለልብ ህመም ያጋልጣል በሚል ሰዎች እንቁላል እንዳይበሉ ሲሰጥ የነበረውን ማስጠንቀቂያ በማስቀረት የእንቁላልን ተፈላጊነት ከፍ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

የጥናት ቡድኑ መሪ የሆኑት ዶክተር ሪክስን፥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንቁላል በጤና በለሙያዎች ዘንድ ያለው ተፈላጊነት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል።

በቅርብ የተሰሩ ሳይንሳዊ ጥናቶችም በእንቁላል ውስጥ የሚገኘው ኮሌስትሮል በደም ውስጥ ባለው የኮሌስትሮል መጠን መጨመር እና ለልብ ህመም ተጋላጭነት ላይ የሚያመጣው ተፅእኖ እንደሌለ እንዳረጋገጡም ዶክተር ሪክስን ተናግረዋል።

በጥናቱ የተገኘው ማረጋጫም እንቁላል በጤናችን ወስጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የሚያመላክት ነው የተባለ ሲሆን፥ በውስጡ በያዘው በርካታ ቫይታሚኖችም ተመራጭ እንዲሆን ያደርገዋል ተብሏል።

ይህም የጤና ባለሙያዎች ለታካሚዎቻቸው የእንቁላል አወሳሰድ መጠናቸውን ጨምሩ ብለው እንዲመክሩ ያበረታታል ተብሏል።

ዶክተር ሪክስን፥ በቅርብ የወጡ የመንግስት መረጃዎች እንቁላል የተፈጥሮ ቫይታሚን፣ ሚነራል፣ ፋቲ አሲድ እና ፕሮቲን ፋርማሲ እንደሆነ ያመለክታሉ ብለዋል።

egg_2.jpg

አንድ መካከለኛ መጠን ያለው እንቁላል 66 ካሎሪዎችን በውስጡ የያዘ ሲሆን፥ 6 ነጥብ 4 ግራም ፕሮቲን በውስጡ ይዟል።

በእንቁላል ውስጥ ያለው የተመጣጠነ የአሚኖ አሲድ ንጥረ ነገርም ሰዎች በቀላሉ ውፍረታቸውን እንዲቆጣጠሩ እንደሚረዳ ተነግሯል።

ይህም እንቁላል በብዛት ከሰውነት ውፍረት ጋት ተያይዞ የሚከሰተውን ሁለተኛውን አይነት (ታይፕ 2) የስኳር ህመም ላለባቸው ሰዎች ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ያመለክታል።

እንዲሁም እንቁላል የደም ግፊት መጠንን ለመቆጣጠር እንደሚረዳም ተገልጿል።

በመካከለኛ የእድሜ ክልል የሚገኙ ሰዎችም በምግባቸው ውስጥ እንቁላል የሚያካትቱ ከሆነ፥ ለስትሮክ የመጋለጥ እድላቸው በ12 መቶ እንደሚቀንስ ጥናቱ አመልክቷል።

እንቁላልን መመገብ ከእድሜ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችል የጡንቻ መዛልንም እንደሚከላከል ተብራርቷል።

ጥናቱ እንቁላል ከዚህ በተጨማሪም አእምሯችን ጤናማና የዳበረ እንዲሆን ያደርጋል ያለ ሲሆን፥ ከእድሜ ጋር ተያይዞ የሚከሰት የመርሳት ችግርንም እንደሚቀርፍ ጠቁሟል።

ዶክተር ረክስን፥ እንቁላል ውስጥ የሚገኘው ቫይታሚን ቢ ሰውነታችን የተመጣጠነ ጉልበት እንዲያመነጭ ያደርጋል እንዲሁም ነርቮቻችን በአግባቡ ስራቸውን እንዲሰሩ እና ከልክ ያለፈ የሰውነት መዛልን ይከላከላል ብለዋል።

በእንግሊዝ የእንቁላል ኢንዱስትሪ ካውንስል የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለት ይህ ጥናት፥ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ ተመራማሪዎች ተሳፍተውበት ነው የተከናወነው።

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk

በሙለታ መንገሻ