ጥንዶች የሚለያዩባቸው ጉዳዮችና ማስታረቂያ ሃሳቦች

አዲስ አበባ ፣ ሃምሌ 10 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአንድ ሰው ጋር ተዋዶ መኖር ያንን ሰው ማወቅና መረዳትንም የሚያካትት ሊሆን እንደሚገባ የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ጥንዶች አብረው ሲኖሩ ከአካላዊ ግንኙነት በተሻለም ውስጣዊ ግንኙነታቸው ጠንካራና የመረዳዳት ስሜታቸው ፅኑ ሊሆን ይገባል።

ይህ ሁሉ ሆኖ ግን በትዳር/ፍቅር አለም አለመግባባት የሚፈጥሩና ጥንዶቹ የማይስማሙባቸው ጉዳዮች ይኖራሉ።

ጥንዶች በአብዛኛው የማይስማሙባቸው የተለመዱ ጉዳዮችና እነዚህን ልዩነቶች እንዴት መፍታት እንደሚቻል ደግሞ ከዚህ በታች ቀርቧል።

ገንዘብ፦ ብዙ ጊዜ ለልዩነት መነሻው ጉዳይ ገንዘብ እንደሆነ ይነገራል፤ በአያያዝና አጠቃቃም ላይ በሚፈጠሩ ልዩነቶች ሳቢያ።

አንደኛው ወገን ቆጣቢና ወጪን በአግባቡ የሚያወጣ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በተቃራኒው አባካኝ ሆኖ ይስተዋላል።

በዚህ ሳቢያም አለመግባባትና የሃሳብ መለያየት ይፈጠራል።

እንዲህ አይነት አጋጣሚዎች ሲፈጠሩ ደግሞ መጨቃጨቅ ሳይሆን በሰከነ መንፈስ መወያየትና መግባባትን አስቀድሙ።

በዚህም የገንዘብ አጠቃቀማችሁን በመማከር ስርዓት ማበጀትና፥ አንዳችሁ የተወሰኑ ወጪዎችን ሌላኛችሁ ደግሞ ሌላውን ወጪ ሃላፊነት በመውሰድ መወጣት።

ለቤት ወጪዎች ገንዘብ ማውጣት ከመጀመራችሁ በፊትም፥ እኔ ይሄን አንች ደግሞ ቀሪውን በሃላፊነት እንወጣ በማለት መከፋፈልና በዚያው መመራት።

የቤት ወጪዎችን በጋራ በመሸፈንም የሚፈጠር ብክነትን ማስቀረት።

በአብሮነት የምታሳልፉት ጊዜ፦ አንዳንድ ጊዜ ከባለቤቴ/ ፍቅረኛየ ጋር ላሳልፈው የሚገባኝን ያክል ጊዜ አላሳለፍኩም አልያም በተቃራኒው ብዙ ጊዜ አብረን አሳልፈናል በሚል ሊያስቡ ይችላሉ።

በዚህ መሃል አብራችሁ ጊዜ ማሳለፍ ፈልጋችሁ፥ አንዳችሁ ባለፈው አሳልፈን አሁን እንኳን የራሴ ጊዜ ይኑረኝ በማለት አለመግባትና የሃሳብ ልዩነት ሊፈጠር ይችላል።

ይህ ሲሆን ግን አንድ ላይ ጥሩ ጊዜ ታሳልፉ ዘንድ ለእናንተ የተሻለውን ጊዜና ሰዓት መምረጥና መወሰን።

በዚያ መልኩ ፕሮግራማችሁን ማስኬድ፥ ያን ስታደርጉ ግንኙነታችሁም ዘላቂ ይሆናል።

ስሜትን መቆጣጠር፦ በፍቅር ውስጥ አንደኛው የአንደኛውን ወገን ስሜት መቆጣጠርና መረዳት ካልቻለ ለዘለቄታው እንቅፋት ይሆናል።

አንደኛው ወገን ተሰሚነቱ እንደቀነሰ ሲያስብ በሌላኛው ወገን ደግሞ የፍቅር አጋሬ ከሚገባው በላይ ስሜዊነት ይታይባታል በሚል በተለያየ ሃሳብ መንጎድ ሲከሰት ይስተዋላል።

ይህ ደግሞ በጥንዶቹ መካከል አለመግባባትን በማስፈን ልዩነትን ይፈጥራል።

በዚህ ጊዜ ሁለታችሁም በየስሜታችሁ ከመነዳትና የራሳችሁን ብቻ ከማዳመጥ፥ የሁለታችሁንም ልዩነት በደንብ ሊያስተውል የሚችል የቅርብ ወዳጅን መጥራትና በጉዳዩ ላይ በጋራ መማከር የተሻለው ይሆናል።

ቤት ውስጥ የአጋርን ቤተሰብን ማስተናገድ፦ በአንዳንድ ጥንዶች ዘንድ የትዳር/ፍቅር አጋርን ቤተሰብ ለቀናትም ቢሆን ቤት ውስጥ ማስተናገድ ለፍቅር ጠንቅ ይሆናል የሚል እሳቤ አለ።

ወላጅ ቤታችሁ ውስጥ ሊጠይቅ ሲመጣና ከእናንተ ጋር ለማሳለፍ ቤታችሁ ጎራ ሲል በራሳችሁ ጉዳይ ስለምትጠመዱ ችላ ትላላችሁ።

በዚህ ጊዜ ወላጅ ችላ የተባለበት ወገን ነገሮችን ከክፋት ማየትና ወላጆቹ በአጋሩ ዘንድ እንዳልተፈለጉ ሊያስብ ይችላል።

ይህ ሁኔታም በርካታ ጥንዶችን ለችግር ሲዳርግ ተስተውሏል።

ይህ ከመሆኑና ወደ ግጭት ውስጥ ከመግባታችሁ በፊት ግን ጥንዶች ቢነጋገሩ መልካም መሆኑን የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ይብዛም ይነስ ብቻችሁን አትኖሩምና ወላጅን ቤታችሁ ጠርታችሁ ከእናንተ ጋር ጊዜ እንዲያሳልፍ መጋበዝ ስታስቡ ተነጋግራችሁ በጊዜው ላይ መወሰንም ይኖርባችኋል።

የልጆች አያያዝ፦ ይህ ደግሞ በጣም የተለመደውና ዘወትር በትዳር አጋሮች ዘንድ ልዩነት የማይጠፋበት ጉዳይ ነው።

ወላጆች ልጆች እንዴት መያዝ አለባቸው በሚለውና ሲያጠፉ እንዴት ይቀጡ የሚሉ ጉዳዮችም ያጨቃጭቋቸዋል።

ይህ ግን ልምድ ካልሆነ የከፋ ልዩነት አያመጣምና ልጆችን በጋራ እሳቤ ለማሳደግና የሚያስፈልጓቸውን ነገሮችም በዚያው ልክ መከወን ይልመዱ መልዕክታቸው ነው።

 

 

 

 

 

ምንጭ፦ scienceofpeople.com