በሳንባ ካንሰር የሚጠቁ ቻይናውያን ቁጥር እያሻቀበ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት አስርት አመታት ለሳንባ ካንሰር ተጠቂ የሚሆኑ የቻይና ዜጎች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑ ተጠቆመ።

ለሳንባ ካንሰር ተጠቂዎቹ ቁጥር መጨመር የአየር ብክለት ዋነኛው ምክንያት መሆኑንም ቻይና ዴይሊ ዘግቧል።

የቻይና የህክምና ሳይንስ አካዳሚ ተመራማሪዎች እንዳሉት፥ የሳንባ ካንሰር በተለይም ለበሽታው በቀጥታ ተጋላጭ ባልሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ እየተከሰተ ነው።

ሴቶች እና የማያጨሱ ሰዎችም ለበሽታው በስፋት መጋለጥ ሲጋራ ማጨስ ብቻ የሳንባ ካንሰር ምክንያት አለመሆኑን ያሳያል ብለዋል።

በቻይና ከ300 ሚሊየን በላይ ህዝብ ሲጋራ እንደሚያጨስ ይነገራል።

የአካዳሚው መረጃ ግን ባለፉት 10 እና 15 አመታት እየታየ ያለው ከፍተኛ የሳንባ ካንሰር ተጋላጭነት ከሲጋራ ማጨስ ጋር የተገናኘ አይደለም ይላል።

አደገኛ የአየር ብክለትን ለማስወገድ ዘመቻ ላይ የምትገኘው ቤጂንግ፥ በተለይም ኢንዱስትሪ በሚበዛባቸው ሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል የአየር ብክለቱ ለጤና አስጊ መሆኑ ተጠቁሟል።

በያዝነው የፈረንጆቹ አመት መጀመሪያ በብሪቲሽ ጆርናል ላይ የታተመ ጥናት ቻይና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያስቀመጠውን መመሪያ ተግባራዊ አድርጋ የአየር ብክለትን መቆጣጠር ብትችል በየአመቱ በለጋ እድሜያቸው የሚቀጩ 3 ሚሊየን ሰዎችን ህልፈት መታደግ እንደምትችል አመላክቷል።

ቻይና በ2015 በካንሰር ላይ በጀመረችው የሶስት አመት ዘመቻ ዜጎችን ለካንሰር በማጋለጥ ረገድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉልህ ድርሻ እንዳለው የሀገሪቱ መንግስት ደርሼበታለሁ ብሏል።

ካንሰር ሩብ ለሚሆነው የቻይና ህዝብ ህልፈት ምክንያት በመሆኑ በሀገሪቱ የጤና ስርአት ውስጥ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል።

በርካታ ጥናቶችም የአየር ብክለት እና ካንሰር ግንኙነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል።

ባለፈው አመት በሄቤይ ዩኒቨርሲቲ የተደረገ ጥናት በሀገሪቱ በሳንባ ካንሰር የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንደ አውሮፓውያኑ ከ1973 እስከ 1975 ከነበረበት ከ2010 እስከ 2011 በሶስት እጥፍ ማደጉን አሳይቷል።

በከተሞች ከፍተኛ የውሃ ብክለት እና የኬሚካል ማዳበሪያዎች እና ፀረ ተባዮች ፍጆታ ለካንሰር ተጠቂዎች ማሻቀብ ሌላኛው ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል።

 

 

 

ምንጭ፦ ፕረስ ቲቪ

 

 

 


በፋሲካው ታደሰ