የአልኮል ጥገኝነትን የሚያሳዩ 10 ምልክቶች!

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 5፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአሁኑ ወቅት በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሚያስፈልጋቸው በላይ አልኮል እንደሚወስዱ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የመጠጥ ፍጆታቸውን መቀነስ አልያም ማቆም የሚያዳግታቸውም በርካታ ናቸው ነው የሚሉት።

ከልክ ያለፈ መጠጥ ጉበታችን ብቻ አይደለም የሚጎዳው፤ አጥንት እና የአዕምሮ ህዋሳቶች ላይም ጉዳት ያደርሳል።

መጠጥ ለድብርት፣ ለትዳር ፍቺ እና ስራ ማጣትም ሲዳርግ ይስተዋላል።

ብዙዎቻችን የምንጠጣው ነገር ምን ያህል የአልኮል መጠን እንዳለው የማናውቅ መሆኑና የጠጣነውን መጠን ቀንሰን የመናገር ልማድ እንዳለን ነው ዶክተር ኢቅባል ሞሂዩዲን የተባሉ የአዕምሮ ሀኪም የሚናገሩት።

“ብዙ ጊዜ ያጋጠሙኝ ሰዎች ምን ያህል አልኮል እንደወሰዱ ስጠይቃቸው የሚነግሩኝ ከተጠቀሙት በግማሽ አሳንሰው ነው” የሚሉት ዶክተር ሞሂዩዲን፥ ይህም የመጠጦችን የአልኮል ይዘት ካለማወቅ ሊመጣ እንደሚችል ተናግረዋል።

ከ20 በመቶ በላይ አሜሪካውያን እና ብሪታንያውያን ከልክ ያለፈ አልኮል እንደሚወስዱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

አንዳንድ ሰዎች የአልኮል ፍጆታቸውን በፍጥነት ማስተካከል ሲችሉ ሌሎቹ ከአልኮል መላቀቅ ከብዷቸው ለአልኮል ጥገኛ ይሆናሉ።

በለንደን የሮያል የአዕምሮ ጤና ኮሌጅ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት 10 ነጥቦች የአልኮል ፍጆታችን አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ያሳያሉ ተብሏል።

1. አልኮልን ከንዴት፣ ፍርሃት እና ድብርት ብቸኛ መውጫ መንገድ አድርጎ መጠቀም

2. ምንጊዜም በራሳችን የምንተማመነው አልኮል ስንወስድ ብቻ ነው ብሎ ማሰብ

3. የመጠጥ ልማዳችን ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ሲያበላሽ፤ “ስትጠጣ ብዙ ጊዜ ትነጫነጫለህ፤ ፀባይህ ይቀያየራል” የሚሉ አስተያየቶች የሚሰነዘሩ ከሆነና ስንጠጣ አብረውን ያሉ ሰዎች ምቾት ሲያጡ፣ በእኛ ሲያፍሩ

4. ሌሎች ተግባራትን ትተን አልኮል ለመጠጣት ሰፊ ጊዜ መስጠት

5. አልኮል በስራ፣ ቤተሰብ እና የፍቅር ግንኙነት እያደረሰብን ያለውን ተፅዕኖ ወደኋላ በመተው መጠጣትን መቀጠል

6. የምንጠጣውን አልኮል መጠን ሁልጊዜ ከጓደኞች እና ቤተሰቦች መደበቅ

7. ከጠጣን በኋላ የምንበሳጭ፣ የምንናደድ እና ራሳችን የማጥፋት እቅድ የሚኖረን ከሆነ፤ ነገር ግን በሌላኛው ቀን ተመልሰን ወደ መጠጥ ቤት ጎራ ካልን

8. በማለዳ አልኮል የመጠጣት ልማድ

9. ጠጥተን ባደርንበት እለት ማግስት የመንቀጥቀጥ እና የፍርሃት ስሜት

10. በስአታት እና በቀናት የውስጥ ያከናወንናቸውን ተግባራት መዘንጋት

 


ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk/

 

 


በፋሲካው ታደሰ