አለርጂ እንዴት ሊከሰትና ልንከላከለው እንችላለን?

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በዓለም ዙሪያ አለርጂ በሚያስደነግጥ አኳሃን እየተስፋፋ ይገኛል።

በአሁኑ ወቅት 300 ሚልየን የሚጠጋ ሰው በአስም ይሰቃያል፣ በምግብ አለርጂ የሚሰቃዩ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ200 እስከ 250 ሚሊየን ይደርሳል።

ከዓለማችን ህዝብ ውስጥ 10 በመቶው በመድሃኒት አለርጂ ይሰቃያል።

የዓለም የአለርጂ ድርጅት( WAO)፥ የአለርጂ በሽታ ተጋላጭነት በአደጉትም ሆነ በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት በመጨመር ላይ መሆኑን አስታውቋል።

ከዛፍ ላይ የሚወርዱ ብናኞች፣ ምግብ፣ አቧራ፣ የእባብ ወይም የእንስሳት መርዝ እና እንደ ድመቶች፣ ውሾች እና በረሮዎች ለአለርጂ በሽታ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው።

ሰውነታችን ከእነዚህ ነገሮች ውስጥ አንዱ ሲያጋጥመው ሰውነታችን እንደ ስጋት በመውሰድ በስህተት ሰውነትን የበሽታ መከላከያ አቅምን ያንቀሳቅሳል ይላሉ ባለሙያዎች።

እነዚህ ጎጂ ላልሆኑ ነገር ግን በዙሪያችን ለሚገኙ ነገሮች ሰውነታችን በሽታን የመከላከል ስርዓቱን ሲያንቀሳቅስ አለርጂ እንደሚከሰትም ነው የሚያነሱት።

አለርጂ በሰዎች ላይ በተለያየ መልኩ የሚከሰት ሲሆን፥ የከፋ ህመም በሰዎች ላይ የሚያስከትሉም አሉ።

በተለይ የምግብ አለርጂ እና አስም የመሰሉት በህይወት ላይ ጉዳይ የማድረስ አቅም ያላቸው ናቸው።

ሰዎች አንድ ጊዜ በአለርጂ ከተያዙ በህይወት ዘመናቸው አብሯቸው ሊቀጥል እንደሚችል የሚያነሱት ባለሙያዎቹ፥ አለርጂዎችን ማስወገድ፣ የታዘዙ መድሃኒቶችን በትእዛዙ መሰረት መውሰድ እና በአለርጂ ወቅት እንድንተገብር የሚገባውን የባለሙያ ምክር በአግባቡ ማወቅ ራሳችንን ለማከም ያግዛል ብለው ይመክራሉ።

 

 

 


ምንጭ፦ medicalnewstoday.com