በተደጋጋሚ ሲነገሩ ውጥረት ላይ መሆንዎን የሚያመላክቱ ቃላት

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አንዳንድ ቃላት በተደጋጋሚ ሲነገሩ ውጥረት እንደተሰማዎት ሊያመለክቱ እንደሚችሉ አንድ የአሜሪካ ጥናት አስታውቋል።

ጥናቱን ያቀረበው አንድ የንግግር ባለሙያዎች ቡድን እንደሚለው፥ አንድ ሰው በተጨነቀ ጊዜ እንደ "በትክክል"፣ "እና ወይም ስለዚህ" እንዲሁም "በጣም" ያሉ ቃላትን ይጠቀማል።

በተጨማሪም ተመራማሪዎቹ ውጥረት ላይ ያለ ሰው ቀስ ብሎ እንደሚናገር ጠቁመዋል።

በብሔራዊ ሳይንስ አካዳሚ ሂደቶች የታተመው ይህ ጥናት፥ የ143 በጎ ፈቃደኞች የንግግር ዘይቤን በመመርመር በእያንዳንዱ ደቂቃ በሁለት ቀናት ውስጥ የድምፅ ቀረፃን ይደረግ ነበር ብሏል።

በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ማቲየስ ሜህል፥ በተደጋጋሚ የሚነገሩ ቃላትን እና መግለጫዎችን በማዳመጥ የተቀዱትን በመተርጎም ይጠኑ እንደነበር ገልጸዋል።

በዚህ ጥናት በተለይ በበጎ ፈቃደኞች የሚነገሩ ተውላጠ ስሞች እና ቅጽል ስሞች አጠቃቀም ትኩረት ይደረግ እንደነበር ተነግሯል።

ተመራማሪው ማቲየስ ሜህል እንመደሚሉት፥ እነዚህ ቃላት ጥናት እየተደረገባቸው ባሉት ሰዎች ምንም ትርጉም የሌላቸው ቢሆኑም ምን እንደሚፈፀሙ ግን ያሳዩ ነበር።

ቀጥሎም ባለሙያዎቹ በተሳታፊዎች የነጭ የደም ህዋሶች ውስጥ ያለውን የበራሂ (gene) አገላለጽ በመመልከት፥ የተሳታፊዎችን የስነ-ልቦና ውጥረት ደረጃዎች መለካት ችለዋል።

በግኝቱ የተጨነቁ ተሳታፊዎች ተውሳከ ግሶችን (የግስ ጭማሪ ቃላትን) የመጠቀም ዕድል ከማሳየታቸው ባሻገር፥ እንደ "የእነሱ" እና "እነሱ" የመሳሰሉ የሶስተኛ ወገን ብዙ ቁጥር የሚያሳዩ ቃላት የመጠቀም ዕድላቸው አነሰተኛ ነው ተብሏል።

በዚህም ተመራማሪዎቹ እንዳሉት ይህ ሁኔታ ሰዎች ሲጨነቁ በአካባቢያቸው ስላሉት ሳይሆን በራሳቸው ላይ ብቻ ያተኩራሉ።

ተመራማሪዎቹ ይህ የንግግር አቀራረብ የውጥረት ደረጃዎችን የሚያመላክት እንደሚሆን በግኝቱ አረጋግጠዋል።

ይህ ጥናት አዲስ አቀራረብ ቢሆንም፥ ሥነ ልቦናዊ ተፅእኖ በሰዎች ጤንነት ላይ ምን ያህል ተፅእኖ እንደሚኖረው ጥልቅ ግንዛቤ ለማግኘት የሚያስቸል መሆኑ ተገልጿል።

ምንጭ፦ http://www.independent.co.uk