ከሳውና ባዝ የምናገኛቸው የጤና በረከቶች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሳውና በርካታ የጤና አገልግሎቶች ቢኖሩትም በጥናት እስካሁን አልተደገፈም ነበር።

የብሪስተል ዩኒቨርሲቲ በሰራው ጥናት ሳውና ሰዎች ከበሽታ እንዲጠበቁ የመከላከል ሚናው ላቅ ያለ መሆኑን ገልጿል።

በተለይም አካላዊ ህመሞች እንዳይከሰቱ የሚያደርግ ነው ተብሏል።

ሳውና ባዝ በሙቀት አማካይነት ሰውነትን ማከም ሲሆን፥ መነሻውም በፊንላንድ እንደሆነ ይነገራል።

ሰውነትን ለማዝናናት እና ነቃ ለማለት የሚዘወተረው ሳውና ባዝ፥ ከ5 እስ ከ20 ደቂቃ በሚወስድ ጊዜ የሚከናወን ነው።

የሳውና ባዝ ሙቀቱ ከ80 ዲግሪ ሴልሼስ እስክ 100 ዲግሪ ሴልሼስ ይደርሳል።

ሌሎች ሰውነትን በሙቀት የማከም ዘዴዎች ያሉ ሲሆን፥ የቱርክ ባዝ፣ የጨረራ (ኢንፍራርድ) ሳውና፣ ዋኦን ቴራፒ እና ባህላዊው የፊንላንደ ሳውና ተጠቃሾች ናቸው።

በፈረንጆቹ 2015 የምስራቃዊ ፊንላድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ባጠኑት ጥናት የ2 ሺህ 300 ወንዶችን የሳውና ባዝ የመጠቀም የ20 ዓመታት ልማድ በመተንተን የጤና ሁኔታቸውን ገምግመዋል።

በግኝቱም ሳውናን በመደበኛነት የሚያዘወትሩ ሰዎች በልብ ህመም እና በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ የመሞት እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህም ባሻገር ሳውና ባዝ በተከታታይ መጠቀም የአዕምሮ መሳት ስጋትን ቀንሶላቸው ተገኝቷል።

በቅርቡ በተሰራ ጥናት ደግሞ በሳምንት ከአራት እስከ ሰባት ጊዜ ሳውና ባዝ የሚጠቀሙ ሰዎች፥ ለከፍተኛ የደም ግፊት የሚጋለጡበት እድል በ50 በመቶ መቀነሱም ተረጋግጧል ነው የተባለው።

ሳውና የልብ ምትን በማስተካከል እና የደም ቧንቧ ተገቢውን የደም ዝውዝውር እንዲያደርግ የሚረዳ መሆኑም ተጠቁሟል።

በሳውና ባዝ ማድረግ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከማድረግ ያላነሰ የጤና ፋይዳ አለው።

የብሪስተል እና የምስራቃዊ ፊንላንድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በሰሯቸው ጥናቶች፥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን እና ሳውናን አጣምረው የሚያከናውኑ ሰዎች ከሁለቱ አንዱን ብቻ ከሚያዘወትሩት ሰዎች የተሻለ በማንኛውም በሽታ ያለመጠቃት እድል አላቸው።

ሳውና የመገጣጠሚያ ህመሞችን እና መጥፎ ስሜቶችን ለማስወገድ የሚያግዝ ሲሆን፥ ተደጋጋሚ የራስ ምታትን ይቀንሳል ነው የተባለው።

ጉንፋንን ለማስወገድ፣ የሳንባ ስራን ለማቀላጠፍ፣ የአተነፋፈስ ስርዓትን ለማስተካከትል፣ አስምን እና የሳንባ ምችን ለማስወገድ ሚናው ላቅ ያለ መሆኑም በጥናቶች ተረጋግጧል።

 

 

 

 

 

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk