ለሰዎች መልካም ማድረግ ፋይዳው ለራሳችን መሆኑን የሚያሳዩ 6 ምክንያቶች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም የመልካምነት ቀን ዛሬ እየተከበረ ነው።

ቀኑ ዓለም የቅን ሰዎች እና የመልካም ተግባራት ማዕከል እንድትሆን ያለመ ሲሆን፥ ሰዎች እርስ በእርሳቸው እንዲረዳዱም የሚያስገነዝብ ነው።

ለሰዎች መልካም ማድረግ እና የእርዳታ እጅን መዘርጋት በምላሹ ለራሳችን ጥቅም እንደሚያስገኝ የስነ ልቦና እና የማህበረሰብ ሳይንስ ጥናት ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ለዚህም የሚከተሉት ማሳያዎች ቀርበዋል።

1. ደስታን ይሰጣል

አልፎ አልፎ ምንም ጥቅም ሳንጠብቅ ለሌሎች ሰዎች የምናደርጋቸው የበጎነት ተግባራት እኛን ደስተኛ እንድንሆን እንደሚያደርጉ ጥናቶች ያሳያሉ።

ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በ400 ጥናቶች ላይ በሰራው ትንታኔ ደስተኛነትና መልካምነት የምክንያትና የውጤት ተዛምዶ አላቸው።

2. ለጭንቀት የመጋለጥ እድልን ይቀንሳል

በክሊኒካል ስንልቦና ሳይንስ ላይ የሰፈረ አጭር ጥናት፥ በትንሹም ቢሆን በጎ ተግባራትን ለአብነትም በር መክፈትን፣ አቅጣጫ መጠቆምን እና የመሳሰሉትን ለሌሎች የሚያደርጉ ሰዎች ለጭንቀት የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ መሆኑን ያሳያል።

በ77 ሰዎች ላይ በተደረገው ቅኝት በራሳቸው ህይወት ውስጥ ጭንቀት ሲያጋጥማቸው፥ ለሌሎች እርዳታ በሚያደርጉበት ጊዜ የተጨናነቁበት መጥፎ ነገር እንደሚቀንስላቸው ጠቁመዋል።

3. ለልብ ጤንነት መልካም ነው

በጎነት ወይም መልካምነት አዕምሮ እንዲነቃቃ እና ኦክሲቶሲን የተባለውን መልካም ስሜት የሚሰጥ ሆርሞን እንዲመነጭ ያደርጋል ይላሉ የተለያዩ ጥናቶች።

የዚህ ኬሚካል መመንጨት ሌላው ፋይዳው የልብ ስርዓትን ማስተካከል ነው።

ዶክተር ዴቪድ ሃሚልተን ሳይንቲስት እና “Why Kindness is Good For You” የሚል መፅሃፍ ደራሲ ናቸው።

እሳቸው እንደሚሉት ኦክሲቶሲን ሆርሞን ናይትሪክ ኦክሳይድ የተባለ ንጥረ ነገር በደም ቧንቧዎች ላይ እንዲለቀቅ ያደርጋል፤ ይህ ደግም የደም ቧንቧ እንዲለጠጥ ያግዘዋል።

ይህም የደም ግፊትን እንዲቀንሰ የሚያደርገው በመሆኑ ኦክሲቶሲን “የልብ ስርዓት ጠባቂ ሆርሞን” ተብሎ ይጠራል ነው ያሉት ዶክተር ዴቪድ።

4. በወጣትነት ለመቆየት ያስችላል

የካልፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በሰራው ጥናት በጎነት የሰው ልጅ የነርቭ ስርዓት ንቁ እንዲሆን ያደርጋል።

በተለይም ቬገስ የተባለው ነርቭ የልብ ምትን ከመቆጣጠር ባሻገር በሰውነታችን ውስጥ ባዕድ ነገሮችን ይቆጣጠራል።

በሰውነታችን ውስጥ ከፍተኛ የህመምና የማቃጠል ስሜት የአካላችን እርጅና ሊጠቁም ይችላል።

ጥናቱ በጎ ተግባራትን ለሌሎች ሰዎች ማድረግ ካልተገባ እርጅና ለመጠበቅ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው ብሏል።

5. የማህበራዊ ህይወት ፍራቻ ላለባቸው ሰዎች መልካም ተግባርን ማከናወን ጥሩ ነው

የተለያዩ ጥናቶች የማህበራዊ ህይወት ፍራቻ ያለባቸው ሰዎች ለሌሎች መልካም ተግባራን ቢያከናውኑ ችግሩ እንደሚስተካከል ይጠቁማሉ።

የኮሉምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ሰዎች በማህብራዊ ህይወት ውስጥ ያለመሳተፍ ችግር ካለባቸው፥ ትናንሽ መልካም ተግባራትን ቢያከናውኑ ለአብነትም ለሌሎች ሰዎች በር መክፈትን፣ ለጓደኞቻቸው ምሳ ቢጋብዙ፣ መጠነኛ በጎ አድራጎት ቢደርጉ ወዘተ ችግራቸው ይስተካከላል ብለዋል።

የጥናት ቡድኑ መሪ ዶክተር ሊን ኤልደን እንድተናገሩት፥ መልካምነት ወይም በጎነት በማህበራዊ ህይወት ውስጥ ለመሳተፍ ያለንን ፍራቻ በማስወገድ አዎንታዊ ነገሮችን ለማጎልበት ይጠቅማል።

6. በጎነት ከአንዳችን ወደ ሌላው የሚተላለፍ ማህብራዊ እሴት ነው

እኛ ቅን ከሆንን ሌሎችን ቀና እንዲሆኑ እናነሳሳቸዋለን።

በፈረንጆቹ 2010 በካሊፎርኒያ፣ ሳንዲየጎ እና ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲዎች የተዘጋጀ አንድ ጥናት፥ በጎነት ወይም መልካምነት ለውጥ የሚያመጣ ማህበራዊ እሴት መሆኑን ይፋ አድርገዋል።

በጥናታዊ ምልከታቸው አንድ ሰው ሌሎችን ለመርዳት ገንዘብ በሚሰጥበት ጊዜ ወይ ከሌሎች ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ በሚሆንበት ጊዜ፥ ድጋፍ ተቀባዮቹ በሌላ ጊዜ ገንዘባቸውን ወይም ጉልበታቸውን ሌሎችን ለመርዳት እንዲያውሉት ያነሳሳቸዋል ነው ያሉት።

መልካም ሰብዕና ከአንዱ ወደ ሌላው ሰው የሚተላለፍ እሴት ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ፥ በተለይም መልካምነት በጎ ነገርን ከትውልድ ወደ ትውልድ ወይም ከጓደኛ ወደ ጓደኛ ለማሸጋገር ያለው ሚና ትልቅ እንደሆነ ገልፀዋል።

 

 

 

ምንጭ፦http://home.bt.com