ያለ እድሜ የሚከሰቱ ራሰ በራነትና ሽበት የልብ ህመም ተጋላጭነት ምልክቶች ሊሆኑ ይችላሉ- ተመራማሪዎች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 26፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች እያለ ለራሰ በራነት የተጋለጡ እና ሽበት ያበቀሉ ወንዶች ለልብ ህመም የተጋለጡ መሆኑን ሊያመላክት እንደሚችል ተመራማሪዎች ጠቁመዋል።

ተመራማሪዎች በህንድ በሚኖሩ ከ2 ሺህ በላይ ወጣት ወንዶች ላይ ባካሄዱት ጥናት፥ “coronary artery” ለተባለው የልብ ህመም የተጋለጡ ወንዶች ጤነኛ ከሆኑት ጋር ሲነፃፀሩ ያለ እድሜያቸው የተከሰተ ራሰ በራነት ወይም ሽበት እንደሚከሰትባቸው ለይተዋል።

ጥናቱ እድሜያቸው ከ40 ዓመት በታች የሆኑ 790 “coronary artery” ለተባለው የልብ ህመም የተጋለጡ እና 1 ሺህ 270 ጤነኛ ወንዶች ላይ ነው የተካሄደው።

የሁሉም ተሳያፊዎች የህክምና ታሪክ የተወሰደ ሲሆን፥ ለራሰ በራነትና ሽበት የተጋለጡ ወድነዶች በተመሳሳይ ደረጃ ላይ የፀጉር መሳሳትና የሽበት መንስኤዎች እንዲሁም መጠኑ ታይተዋል።

ተመራማሪዎቹ ያገኙትን ግኝት ከልብ ህመም ምልክቶች ጋር በማዛመድ አንድ ላይ ለመመልከት ሞክረዋል።

በዚህም ለልብ ህመም የተጋለጡ ሰዎች ያለ እድሜ ለሚከሰት ሽበት የመጋለጥ እድላቸው በ50 በመቶ ጨምሮ የታየ ሲሆን፥ ጤነኛ የተባሉት ቡድን ላይ ግን ራሰ ሽበት የመከሰት እድሉ 30 በመቶ ብቻ ነው።

ከልብ ጋር የተያያዘ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች ለራሰ በራነት የመጋለጥ እድላቸው በ49 በመቶ ጨምሮ የታየ ሲሆን፥ የጤነኞች ተጋላጭነት ግን 27 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል።

በጥናቱ ላይ የተሳተፉት ዶክተር ካማል ሻርማ፥ “ለዚህ አሳማኝ ምክንያት ሊሆን የሚችለው ባዮሎጂካል እድሜ ነው፤ ምክንያቱም ባዮሎጂካል እድሜ በአንዳንድ ታማሚዎች ላይ ፈጣን ሆኖ ይታያል፤ ይህ ደግሞ ራሰ በራነት እና ሽበት ያለ እድሜ እንዲከሰት ያደርጋል” ብለዋል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2013 በጃፓን በሚኖሩ 37 ሺህ ሰዎች ላይ በተካሄደ ጥናት በወንዶች ላይ ከሚከሰተው ራሰ በራነት ውስጥ 32 በመቶ ያክሉ ከልብ የጤና ችግር ጋር ሊያያዝ እንደሚችል መጠቆሙ ይታወሳል።

በአውሮፓውያኑ በ2014 በዴንማርክ የተካሄደ ጥናትም በወንዶች ላይ ያለ እድሜ የሚከሰት ሽበት የወንዶችን የወደፊት የልብ ጤንነት ሁኔታን ሊጠቁም እንደሚችል ማመልከቱ አይዘነጋም።

የጥናት ቡድኑ መሪ ዶክተር ደሃምዲፕ ሁማኔ፥ ያለ እድሜ ለሚከሰት ራሰ በራነት እና የፀጉር በሸበት የተጋለጡ ወንዶች ተጨማሪ የልብ ጤንነት ምርመራዎችን ቢያካሂዱ መልካም መሆኑን ይመክራሉ።

እንዲሁም ጤናማ የሆነ አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በመስራት እና መሰል ነገሮችን በማድረግ የአኗኗር ዘይቤያቸውን እንዲያስተካክሉም መክረዋል።

የልባችንን ጤና እንዴት ማሻሻል ይቻላል…?

vegetables.jpg

በእለት ምግባችን ውስጥ አትክልትና ፍራፍሬን ማካተት

ሲጋራ ማጨስ ማቆም

ሁሌም ንቁ መሆን እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መስራት

የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር

በፋይበር የበለፀጉ ምግቦችን አዘውትሮ መመገብ

ስብ የበዛባቸውን ምግቦች መጠን ቀንሶ መውሰድ

በምግባችን ውስጥ የምንጠቀመውን የጨው መጠን መቀነስ

አሳ መመገብ

የአልኮም መጠጣት ማቆም ወይም አወሳሰዳችንን በመጠኑ ማድረግ

ምንጭ፦ www.bbc.com