ምቾት ያለው እንቅልፍ መተኛት ለጤና የሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 27፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ምቾት ያለው እንቅልፍ የሚባለው በሰዓት ሲገለፅ ቢያንስ ከስምንት ሰዓት በላይ ሰላማዊ እንቅልፍ መተኛት ነው።

ይህ ሲባል ሌሊቱ የተረጋጋ፣ ንፁህ እና እንቅልፍ የሚረብሽ ምንም አይነት ድምፅ የማይሰማበት ሲሆን ነው ይላሉ ባለሙያዎች።

ጥራት የሌለው እንቅልፍ የጭንቀት መጨመር፣ የክብደት መጨመር እና የምግብ መፍጨት ስርአትን ያዛባል።

የእንቅልፍ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ኔይል ስታንሌይ፥ ከመጥፎ የሌሊት እንቅልፍ የሚገኝ ምንም ጥሩ ነገር የለም ብለዋል።

ዶክተር ስታንሌይ ከአንድ ምሽት ጥራት የሌለው እንቅልፍ በኋላ የጤና እክል የሚያስከትሉ የበለጠ ስኳር እና ቅባት ያላቸው ምግቦችን ፍላጎት መጨመርን እንዲያመጣ ተናግረዋል።

ሰላማዊ ያልሆነ እንቅልፍ ከቤተሰብ ጋር መልካም ያልሆነ ግንኙነት እንዲኖር እና ከስራ ባልደረቦች ጋር ግጭት ያስከትላል፤ የትራፊክ አደጋ የማጋጠም እድል ከፍተኛ እንዲሆን ያደርጋል ነው የሚሉት።

ከዚህ ባለፈ ደካማ የእንቅልፍ ሁኔታ የስኳር በሽታ፣ የልብ ህመም፣ ድብርት እና ከመጠን በላይ የሆነ ውፍረት ማስከተል የረጅም ጊዜ የጤና ችግሮችን ይፈጥራል።

ዶክተር ኔይል ስታንሌይ "ሰዎች ስለ አመጋገብ ያስባሉ፣ ባለብዙ ቫይታሚን ምግብ ይወስዳሉ፣ ቀላል የሰውነት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ፣ የፊት ክሬም ይገዛሉ፤ በእነዚህ ነገሮች ላይም ብዙ ጊዜ እና ገንዘብ ያጠፋሉ። ነገር ግን እንቅልፍን እንደ አስፈላጊ ነገር አይገነዘቡም። ስለዚህ ማንኛውንም ነገር ካደረግን በኋላ ምቾት የላው እንቅልፍ ማግኘት የጤና ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፤” ብለዋል።

ጤና_1.jpeg

ለዚህም በመጀመሪያ ደረጃ በአንድ ምሽት በአማካይ ስምንት ሰአት በጥሩ እንቅልፍ ማሳለፍን ቅድሚያ መስጠት አለብዎት ሲሉ መክረዋል።

በሁለተኛ ደረጃ ጨለማ፣ ፀጥ ያለ፣ ቀዝቃዛ እና ለመተኛት ምቹ የሆነ መኝታ ቤት ቢኖርዎ መልካም ነው።

ለዚህም ከመተኛትዎ በፊት ቢያንስ ከ45 ደቂቃዎች አስቀድሞ ቴሌቪዥን፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮች እና ታብሌቶችን መዝጋት ያስፈልጋል።

በመጨረሻም ሌሊቱን በሰላም ተኝቶ ለማሳለፍ በጣም አስፈላጊ ነገር ግን ያልተለመደው ሰላማዊ አእምሮ ነው፤ ይህ ማለት ውጥረት ሲያጋጥምዎ ወይም ሲጨነቁ መተኛት አይችሉም።

ስለዚህ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥምዎ ከመተኛትዎ በፊት ሁልጊዜ ማታ ማታ መፅሀፍ የማንበብ ልምድ ቢኖሮዎት ይመከራል ሲሉ ባለ ሙያዎች ይናገራሉ።

በአጠቃላይ ደስተኛ እና ጤናማ ህይወት ለመኖር ከፈለጉ ለጥሩ እንቅልፍ ቅድሚያ መስጠት ይኖርብዎታል ተብሏል።

 

ምንጭ፦http://www.huffingtonpost.co.uk