ተመራማሪዎች በቀኝ ጆሮ መስማት ጉዳዩን የተሻለ ለመረዳት እንደሚያግዝ ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 28 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) ያዳመጡትን አልያም ከሰዎች ጋር የተነጋገሩትን ንግግር በአግባቡ ማስታወስ ብዙ ጊዜ አስቸጋሪ ሲሆን ይስተዋላል።

ተመራማሪዎች ደግሞ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሰዎች በየትኛው የጆሮ ክፍላቸው ቢሰሙና ቢያዳምጡ ነው የተሻለ ማስታወስና መገንዘብ የሚችሉት በሚለው ጉዳይ ላይ ጥናት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ከሰሞኑም ታዲያ ይህን የጥናታቸውን ውጤት ይፋ አድርገዋል።

በዚህ መሰረት ሰዎች ከግራ ጆሯቸው ይልቅ በቀኝ ጆሯቸው ቢሰሙና ቢያዳምጡ የተሻለ መገንዘብና ነገሮችን ማስታወስ ይችላሉ ነው ያሉት ተመራማሪዎቹ።

በግራ ጆሯቸው የሚሰሙትን ነገር ችላ ማለትና በቀኛቸው ብቻ ለማዳመጥ መሞከሩም ንግግሩን አልያም ድምጹን በ40 በመቶ የተሻለ የመረዳት እድል ይፈጥርላቸዋልም ነው ያሉት።

በአላባማ ኦበርን ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተመራማሪዎች በተለይም ህጻናትና አዋቂ እድሜ ላይ የደረሱ ሰዎች በአብዛኛው በቀኝ ጆሯቸው የሚሰሟቸውን ነገሮች የተሻለ መረዳትና ማስታወስ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ከግራ ጆሮ ይልቅ በቀኝ ጆሮ መስማትና ማዳመጥ ነገሩን በ40 በመቶ የተሻለ ለመረዳት ያግዛል።

ተመራማሪዎቹ ከህጻናት እስከ አዋቂ አደረግነው ባሉት ጥናት፥ ንግግሩን ለማስታወስ የሚያግዱ ሌሎች ከባቢያዊ ምክንያቶችንም ከግምት አስገብተናል ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም እድሜና ሌሎች የጤናና ተዛማጅ ጉዳዮችን አካተው ምርምሩን ማድረጋቸውንም ነው የገለጹት።

የጥናቱ ተሳታፊዎች በሁለቱም ጆሮዎቻቸው የተለያዩ ድምጽና አረፍተ ነገሮችን እንዲሰሙና የሰሙትንም ለየብቻ ነጣጠለው እንዲያዳምጡም ተደርጓል።

ሁለቱም ጆሮዎች ለየብቻ የሰሙትን ድምጽ በአንድ ላይ እንዲያስታውሱ የማድረግ ስራ መስራታቸውንም ተመራማሪዎቹ ይናገራሉ።

በዚህ ጊዜ ህጻናትና ታዳጊዎቹ ነጣጥለው መስማት ሳይሆን በቀኝ ጆሯቸው የሰሟቸውን ነገሮች የተሻለ መረዳት መቻላውን ነው የተነገረው።

በእነዚህ መንገዶች የተገኘው ውጤትም ሰዎች ከግራ ይልቅ በቀኝ ጆሯቸው ሲሰሙ የተሻለ መረዳትና መገንዘብ እንዲሁም ማስታወስ እንደሚችሉ ያሳየ ሆኗል።

በጥናታቸውም አብዛኛው ተሳታፊዎች በቀኝ ጆሯቸው የሰሙትን ነገር በ40 በመቶ የተሻለ መረዳት መቻላቸውን አረጋግጠናል ብለዋል።

እናም በንግግር ወቅትም ሆነ በማንኛወም አጋጣሚ ከግራ ይልቅ ቀኝ ጆሮዎን ጣል አድርገው ቢሰሙ የተሻለ አድማጭ መሆን ይችላሉ፤ የተመራማሪዎች ምክረ ሃሳብ ነው።

 

 

ምንጭ፦ ደይሊ ሜይል