ሳቅ የካንሰር ታማሚዎች ከበሽታው እንዲያገግሙ ይረዳል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 28፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚነገርለት ሳቅ ለካንሰር ታማሚዎችም የሚሰጠው ጠቀሜታ አለው የሚል ጥናት ከሰሞኑ ይፋ ሆኗል።

አዲሱ ጥናት ሳቅ ለካንሰር ታማሚዎች ጥሩ መድሃኒት እንደሆነ ያመለክታል።

በርካታ የካንሰር ታማሚዎች በበሽታው መጠቃታቸውን ተከትሎ ከመጨናነቅ ይልቅ ስም እያወጡለት መዝናናትን እያዘወተሩ መምጣታቸውን የሚጠቁመው ጥናቱ፥ ይህም ለታማሚዎቹ ጥቅም መስጠቱን ነው ያሳየው።

ታማሚዎች በካንሰር ዙሪያ በኢንተር ኔት ላይ የጻፏቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ጽሁፎች ላይ በመመስረት በተካሄደው ጥናት ላይ በርካታ የካንሰር ህሙማን፤ የካንሰር ሴልን “ሴይጣን” ብለው እንደሚጠሩ እና ረጅም ጊዜ የሚወስደውን ህክምና ደግሞ “ማራቶን” ብለው በመሰየም እንደሚዝናኑበት ተለይቷል።

በላንካስተር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድኑ መሪ የሆኑት ዶክተር ሶፊያ ዴምጀን፥ የካንሰር ታማሚዎች ከመጨናነቅ ይልቅ በበሽታው ላይ መቀለዳቸው ከበሽታው ጋር ተያይዞ ከሚከሰት አስከፊ ነገር እንዲያገግሙ ይረዳቸዋል ብለዋል።

ጥናቱ የካንሰር ታማሚዎች በኢንተርኔት ላይ የፃፏቸው ጽሁፎችን በመሰብሰብ መካሄዱን የሚናገሩት ዶክተር ሶፊያ፥ በዚህም በርካታ የካንሰር ታማሚዎች ስለ በሽታቸው እንደሚቀልዱ መለየቱን ገልፀዋል።

በበሽታቸው ዙሪያ የተለያዩ ስሞችን እየሰየሙ የሚልዱ እና የሚስቁ ሰዎች በካንሰር ምክንያት ከሚደርስባቸው ጉዳት በቀላሉ ማገገም ይችላሉ ብሏል ጥናቱ።

ምንጭ፦ www.dailymail.co.uk