ቻይና የአየር ብክለትን በመቀነስ የአካባቢ ንፅህናን በማረጋገጥ ረገድ መሻሻል አሳይታለች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 3፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቻይና ባለፉት አምስት ዓመታት በአካባቢ ንፅህናን ማሻሻል ላይ ያተኮሩ 18 ሕጎችና ደንቦችን በመተግበሯ የአየር ብክለትን በመቀነስ ረገድ እድገት ማሳየቷ ተነገረ።

የሀገሪቱ ብሄራዊ ምክር ቤት እንዳስታወቀው፥ እነዚህ ደንቦች የተሻለ ሥነ ምህዳር በማስፋፋት የሰዎችን መሰረታዊ መብቶችንና ፍላጎቶችን በመጠበቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ምክር ቤቱ በሀገሪቱ የንፁህ አየርና የመጠጥ ውሃ አስፈላጊነት፣ የአካባቢ ጥበቃን ማጠናከር፣ የአካባቢ አየር ብክለት መከላከል፣ የውሃ ብክለት እና የአካባቢን መራቆት የሚመለከቱ ጉዳዮች አንስቶ አይቷል።

በዚህም በያዝነው የፈረንጆች አመት ከዚህ በፊት በወጣው ህግ ተግባራዊ የሆኑ ጉዳዮች በመዳሰስ ችግሮችን በመፍታት ላይ ያተኩራል ነው የተባለው።

በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ ከፋብሪካዎች እና ኢንዳስትሪዎች የሚወጣውን ጭስ ለመከላከልና ችግሩን ለመቀነስ የተደረገውን ጥረት በማስቀጠል አሁንም ይሄን ለማሻሻል ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብሏል።

የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኪ ኪያንግ እንደገለፁት፥ በሀገሪቱ ከፍተኛ የአየር ብክለት የነበራቸው አካባቢዎች ከአውሮፓውያኑ 2013 ጀምሮ 30 በመቶ ቀንሰዋል።

በዚህም በቤጂንግ እና አካባቢው የሚገኙ 13 ከተሞች የሚያገኙት ንፁህ አየር በ2013 በጀት አመት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር 40 በመቶ ያህል መሻሻል አሳይቷል።

በአጠቃላይ ቻይና የአየር ብክለትን በመቀነስ የአካባቢ ንፅህናን ለማሻሻል ያደረገችው እንቅስቃሴ ለውጥ ያሳየ ቢሆንም፥ ነገር ግን አሁንም የአየር ብክለትን ለመከላከልና አካባቢን በመጠበቅ ረገድ ረዥም መንገድ እንደሚጠብቃት ነው የተገለፀው።

ለዚህም አካባቢን፣ የዱር እንስሳትን፣ ውቅያኖሶችን፣ ከባቢ አየር፣ መጠጥ ውሃ፣ የኑክሌር ደህንነት እና የአፈር ንፅህናን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ህጎች በማሻሻል የአየር ብክለትን ለመከላከል መዘጋጀቷ ተነግሯል።

 

 

 

ምንጭ፦ ሲጂቲኤን