ከተመገቡ በኋላ ያስልዎታል?

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሳል ባለንበት አካባቢ ሰውነታችን ከአካባቢያችን የሚረብሸውን ንጥረ-ነገር ለማስወገድ የሚወስደው ምላሽ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ምናልባትም ከተመገቡ በኋላ በተደጋጋሚ የሚያስልዎት ከሆነ መንስዔውን ለማወቅ የህክምና ባለሙያ ማማከር ይገባዎታል፡፡

ከምግብ በኋላ ሳል ሊከሰት ቢችልም የምግብ አለመስማማት፣ አስም፣ የመዋጥ ችግር፣ የሳምባ ምችና ሰውነት ላይ የሚከሰት መመርቀዝ (ኢንፌክሽን) ለዚህ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ተለይተዋል፡፡

የምግብ አለመመቸት፦ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ሊከሰት የሚችል ሲሆን በአብዛኛው በልጅነት ወቅት በተደጋጋሚ ሊከሰት የሚችል አጋጣሚ ነው።

ከምግብ አለመመቸት ጋር በተያያዘ ከተመገቡ በኋላ የሚከሰተው ሳል የሚተነፍሱበትን ጊዜ ርዝመት በማሳጠር የሚመጣ ነው፡፡

ይህ በሚከሰትበት ወቅት ጭንቀት፣ የትንፋሽ መቆራረጥና የአፍንጫ ፈሳሽ መብዛት ያጋጥማል፤ ወተት፣ አኩሪአተር፣ ለውዝ እና እንቁላል ከተመገቡ በኋላ ምናልባት ይህ አጋጣሚ ሊከሰት እንደሚችልም ነው ባለሙያዎች የሚያነሱት፡፡

አስም፦ በመጠጦች ውስጥ የሚገኝ ንጥረ ነገር የአስም መንስዔ ሊሆን ይችላል፤ ቢራ፣ ወይንና ለስላሳ መጠጦች ደግሞ ለዚህ ምክንያት ይሆናሉ ነው የሚሉት ባለሙያዎቹ።

በእነዚህ ምክንያቶች ይህ ሲከሰት ደግሞ፥ ድካም፣ ደረት አካባቢ ምቾት ያለመሰማት እና የተዛባ የአተነፋፈስ ስርዓት ሊያጋጥም ይችላል፡፡

የመዋጥ ችግር፦ የተመገቡት ምግብ ወይም የጠጡት ውሃ ወደ ጎሮሮ ለመውረድ ችግር ሲያጋጥመው ይችህ ችግር ይከሰታል።

በሰውነት ውስጥ የአሲድ መብዛት፦ ይህ የሚከሰተው አሲድ ከሆድ ወደ ምግብ ቧንቧ በሚተላለፍበት ወቅት ከመጠን በላይ ሲረጭ ነው፡፡

በዚህ ጊዜ የምግብ ቧንቧ ላይ የመቆጣት ስሜት ይፈጠራል፤ ይህ ደግሞ መኮምጠጥ ወይንም የመምረር ስሜት፣ የጉሮሮ መቁሰልና የደረት ማቃጠል ያጋጥማል፡፡

የሳምባ ምች፦ ይህ የሚከሰተው ወደ ሰውነት ጠጣር ወይም ፈሳሽ ነገሮች ሲገቡ ሲሆን የጤናማ ሰዎች ሳንባ በሳል አማካኝነት ወደ ውስጥ የገባውን ነገር ሊያስወግደው ይችላል፡፡

ምልክቶቹም ፈሳሽ ያለው ሳል፣ ለመዋጥ መቸገር፣ የምራቅ መብዛት፣ የተቆራረጠ አተነፋፈስ፣ ልብን ማቃጠል፣ ድካም፣ ከምግብ ወይም መጠጥ በኋላ የመታፈን ስሜትና ትኩሳት ናቸው፡፡

መመርቀዝ፦ ይህ የሚያጋጥመው በምግብ ቧንቧ ወይም በማንቁርት አካባቢ ሲሆን መንስዔውም ቫይረስ፣ ፈንገስ እና ባክቴሪያ ናቸው፡፡

በተደጋጋሚ ከተመገቡ በኋላ ሳልና በተጠቀሱት ቦታዎች ላይ የማቃጠልና በአግባቡ የመዋጥ ችግር የሚከሰት ከሆነ ባለሙያ ያማክሩ።

ከተመገቡ በኋላ ሳል የሚያጋጥምዎት ከሆነና ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች በተደጋጋሚ ተከስተው ከሁለት ሳምንት በላይ ከቆዩ ወደ ሃኪም ጎራ እንዲሉ ይመከራል።

 

 

 

 

 

 

ምንጭ፦ ሜዲካል ኒውስ ቱዴይ
ተተርጉሞ የተጫነው፦ አብረሃም ፈቀደ