በፍቅር ህይዎት ውስጥ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 4 ፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በፍቅር ህይወት መነጋገርና ግልጽነት እጅግ አስፈላጊና አብሮነትን ለማዝለቅ ወሳኝ መሆናቸውን የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ካለመነጋገርና ግልጽነትን ካለማስፈን በመነጨ የሚፈጠር መቃቃር መጨረሻው መለያየት ሊሆን እንደሚችልም ነው የሚገልጹት።

ከዚህ በታች ያሉት ደግሞ በፍቅር ህይዎትዎ ሊያጤኗቸውና ቸል ሊሏቸው የማይገቡ ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው።

ችላ ማለት፦ በጣም ቀላሉ ግን ደግሞ አብዛኛዎቹ ጥንዶች የማያስተውሉት ጉዳይ መሆኑን ነው ባለሙያዎቹ የሚናገሩት።

አጋጣሚ ከሁለት አንዳቸው ብቻችን እናውራ የሚል ሃሳብ ሲያቀርቡ፤ “ትንሽ ጠብቂኝ ወይም ጠብቀኝ” ማለት አልያም ቀለል በማድረግ “በኋላ እናድርገው” የሚሉ ምክንያቶች ችላ ማለትዎን ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ።

ይህ ጉዳይ ምናልባት የተጠነሰሰ ትንሽ ኩርፊያ ካለ ጉዳዮን ከፍ ወዳለ መቃቃር ለመውሰድ ምክንያት ይሆናልና ጥቂትም ቢሆን ነገሮችን ችላ ማለት አይገባም።

አለመግባባትና መጨቃጨቅ፦ ሃሳብ ሲለዋወጡም ሆነ በንግግራችሁ መሃል አለመግባባት የሚፈጠርና ነገሮች ወደ ጭቅጭቅ የሚያመሩ ከሆነ ቆም ብሎ ማሰቡ መልካም ነው።

በሃሳብ አለመስማማት ቢኖር እንኳን በንግግር መሃል ጭቅጭቅ አሁንም አሁንም የሚፈጠር ከሆነ ለፍቅር ግንኙነታችሁ አይበጅም።

በንግግር መሃል በሚፈጠር አለመስማማት ወደ ጭቅጭቅ የማምራት ልምድ ካለ ለጉዳዩ እልባት መስጠትና ነገሮችን በሰላማዊ መንገድ የምትፈቱበትን አግባብ ማመቻቸት።

አለመወያየትና ለብቻ መወሰን፦ አብራችሁ እስካላችሁ ድረስ ትንሽም ሆነ ትልቅ ጉዳይ ላይ የምታሳልፉት ውሳኔ የመጨረሻ ውጤት የጋራ መሆኑ አይቀርም።

ምናልባትም ለባለቤትዎ ወይም የፍቅር አጋርዎ ሳያሳውቁ ከነበሩበት በመልቀቅ አዲስ ስራ መጀመርዎ የፈለገውን ያክል እርስዎን ደስተኛ ቢያደርግም ለአጋርዎ ግን የመገለል ስሜትን ይፈጥራል።

ይህን ሲያደርጉ የሄዱበት መንገድም በፍቅር አጋርዎ ላይ የብቸኝነትና የመገለል ስሜትን በመፍጠር በሂደት የመለያየት አጋጣሚን ያሰፋል።

በአንጻሩ እርስዎ ደግሞ በዚህ ምክንያት የሚፈጠር አለመግባባትን በማንሳት፥ የፍቅር አጋሬ ሰላም ነሳኝ/ነሳችኝ የሚል ስሜት ውስጥ በመግባት እያማረሩ ለሰው ያጫውቱም ይሆናል።

ጉዳዩ የቱንም ያክል ይሁን እንጅ፥ የችግሩ መንስኤ በጋራ ቁጭ ብሎ አለመወያየትና ባሳለፉት ውሳኔ ላይ በአጋርዎ ዘንድ የእኔነት ስሜ አለመፍጠርዎ ነው።

እናም በነገሮች ላይ ሊወስኑ ሲነሱ ከአጋርዎ ጋር መወያየትና መነጋገር ከዚያም በጉዳዩ ላይ የተሻለ የጋራ ውሳኔ ማሳለፍን ያዳብሩ።

የባህሪ መቀያየር፦ አንዳችሁ ያንዳችሁን ስሜት የመረዳትና ስሜታችሁን በቀጥታ የማስረዳት ችግር ካለባችሁ ከራስ ጋር የመነጋገር ስሜት ሊፈጠር ይችላል።

ይህ ደግሞ ውስጥን ወደ ማዳመጥና በራስ እሳቤና አካሄድ ለነገሮች ትርጓሜ መስጠትን ይፈጥራል፤ በዚህ ወቅት ታዲያ የባህሪ መቀያየር ይፈጠራል።

ምናልባትም በጋራ ጉዳይ ላይ ከማተኮር ይልቅ በግንኙነታችሁ አልያም በትዳራችሁ እርስዎ ባገኙትና ባጡት ነገር ላይ ማሰብና ሁኔታዎችን በራስ መዝኖ በራስ ምላሽ ወደ መስጠት የማምራት ስሜቱም ከፍ ሊል ይችላል።

መሰል ሁኔታዎች ደግሞ አጋርን ትኩረት ከመንፈግ ጀምሮ የመገናኛም ሆነ የመነጋገሪያ ጊዜ ሊያሳጡ ይችላሉ፤ ይህ ከመሆኑ በፊት ግን መንስኤዎችን መለየትና ወደ መፍትሄ መምጣት።

የበላይነትን ለማሳየት መሞከር፦ በማንኛውም አጋጣሚ የሃሳብ ልዩነት ቢፈጠርም ወደ ተሻለውና አስታራቂ ወደ ሆነው ነጥብ መምጣት እንጅ “እኔ ያልኩት ካልሆነ” በሚል የበላይ ለመሆን መሞከሩ በፍቅር ህይዎት ውስጥ አይመከርም።

በዚህ መሃል የሚፈጠር ጭቅጭቅም አንዱ የበላይ ሌላው ደግሞ የበታች መሆን አልፈልግም ከሚል ስሜት ይመነጫልና በሰከነ መንገድ መወያየቱ ይመከራል።

ከዚያም ያቀረባችሁትን ሃሳብ አንስቶ የተለዋወጣችሁትን ንግግር ማቅረብና በዚያ ላይ መወያየትና ውሳኔ ማሳለፍ መልካም ነው።

ከላይ ከተጠቀሱት ባለፈም አጋርዎን ይረዳኛል ብሎ በማሰብ ከማስረዳት ዝምታን መምረጥ፣ ሳይናገሩ እርሱ/እርሷ እኮ እንዲህ ነው በማለት ተስፋ መቁረጥ፣ በማይሆን ጉዳይ ላይ መጨቃጨቅ፣ ነገሮችን ከአጋርዎ እይታ አንጻር አለመመዘንና ዘወትር እያጠፉ እንነጋገር የሚሉ ልማዶችም ለፍቅር ጠንቆች ናቸው።

እናም በተቻለ መጠን ነገሮችን ከመከወን በፊት ማመዛዘንና ለእያንዳንዱ እንቅስቃሴዎ ትኩረት መስጠትን ባህልዎ ያድርጉ።

 

 


ምንጭ፦ psychologytoday.com