በልጅነታቸው ለርሃብ የተጋለጡ ሰዎች በቀሪው ህይወታቸው ለድብርት ይጋለጣሉ- ጥናት

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 03፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በልጅነታቸው ለርሃብ የተጋለጡ ሰዎች በቀሪው የህይወታቸው ዘመን ለድብርት እንደሚጋለጡ ተመራማሪዎቹ ገለጹ።

በልጅነት ህይወታቸው ለተወሰነ ጊዜ ለርሃብ የተጋለጡ ሰዎች በቀሪ ህይወታቸው ለድብርት አንደሚጋለጡ የጆርጂያ ዩንቨርሲቲ ተመራማሪዎች አመላክተዋል።

በዚህም በይህዎት ዘመናቸው ለድብርት የሚጋለጡ ሰዎች በጽንስ፣ በህጻንነት ወይንም ጉርመስና ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው በፊት በአንድ ወቅት ለምግብ እጥረት ተጋልጠው ሊሆን እንደሚቸል ተጠቁሟል።

ጥናቱ ከቻይና የጤና እና የጡረተኞች ማዕከል በተወሰደ 17ሺህ 708 ቻይናውያን ተጠኝዎች ላይ የተደረገ ሲሆን፥ ተጠኝዎቹ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1959 – 1961 ባሉት 2 ዓመታት በቻይና ተከስቶ በነበረው ከፍተኛ ችግር ተጠቂ የነበሩ መሆናቸው ታውቋል።

ተመራማሪዎቹ እንደገለጹት ከተጠኝዎቹ መካከል ከ25 በመቶ በላይ በህይወታቸው ድብርት የሚሰማቸው መሆኑን የገለጹ ሲሆን፥ 11 በመቶ ያህሉ በልጅንታቸው በቻይና ተከስቶ በነበረው ርሃብ ክፉኛ ተጎድተው የነበረ መሆኑን ገልጸዋል ተብሏል።

በዚህም ተመራማሪዎቹ በተጠኝዎቹ የህይወት ዘመን ለድብርት ከተጋለጡት ተጠኝዎች መካከል 14 በመቶ ያህሉ ከቻይናው ከፍተኛ የርሃብ መከሰት ጋር ተያይዞ የተከሰተ መሆኑን ነው ያመለከቱት። 
ሰዎች በህይወታቸው የመጀመሪያ ምዕራፍ አካባቢ ለርሃብ ሲጋለጡ ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች ሊዛቡ እንደሚችሉና ሰዎቹ ለድብርት እንደሚያጋልጡም ነው በዘገባው የተገለጸው።

ርሃብ፣ የአመጋገብ ችግሮችና ከፍተኛ የድብርት ስሜት ተያያዥነት ያላቸው እና በረጅም ጊዜ በሰዎች ጤና ላይ ከፍተኛ ተጽህኖ ያሳድራሉ ተብሏል።

የጥናቱ መሪና በጆርጂያ ዩንቨርሲቲ የጤና ትምህረት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ቻንጅዌ ሊ በልጂነት ጊዜ ለምግብ እጥረት መጋለጥ በቀሪው የህይወት ዘመን ለድብርት እንደሚያጋልጥ ነው የተናገሩት።

ጥናቱ የስነ ህይወትና ስነ አዕምሮ ጉዳዮች ለድብርት መንስኤ እንደሚሆኑ ያመላከተ ሲሆን፥ ለድብርት መፍትሄ ለማፈላለግና ጤናን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ሌሎች ጥናቶች ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ዘገባው ያመላክታል።

 

ምንጭ፦ scienceblog.com

የተተረጎመውና የተጫነው፦ በእንቻለው ታደሰ