የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካፒታል ለማሳደግ የሚውል የመንግስት እዳ ሰነዶች ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 2 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት እዳ ሰነዶች ወይም ቦንዶች ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ።

ረቂቅ አዋጁ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካፒታል ለማሳደግ የሚውል ገንዘብ፥ በመንግስት እዳ ሰነድ እንዲከፈል ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው የተዘጋጀው ተብሏል።

ረቂቁ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ሲሆን፥ ለዝርዘር እይታ ለበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

በረቂቁ 26 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው የመንግስት ቦንድ እንደሚዘጋጅና፥ ቦንዱ ተከፍሎ ሲጠናቀቅ የሚገኘው ገቢ ለባንኩ ካፒታል ማሳደጊያ ይውላል ነው የተባለው።

የሚዘጋጀው ቦንድም የአምስት ዓመት የችሮታ ጊዜ ኖሮት በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ ነው።

ምክር ቤቱ ከዚህ በተጨማሪም የግሎባል ፈንድ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ሳንባ ነቀርሳን እና ወባን ለመዋጋት የልዩ መብትና ከለላዎች ስምምነት ለማፅደቅ የወጣ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለዝርዝር እይታ መርቶታል።

 


በደመቀ ጌታቸው