የትግራይ ክልል ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ መደበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትግራይ ክልል የሚገኙ ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ከ2 ቢሊየን ብር በላይ በጀት ተመድቧል።

በጀቱ ከፌደራልና ከክልሉ መንግስት የተመደበ ሲሆን ከ400 ሺህ በላይ የክልሉ ወጣቶች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተነግሯል።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጎይቶም ይብራህ፥ በክልሉ በየዓመቱ የዩኒቨርሲቲ፣ የቴክኒክና ሙያ እንዲሁም የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 150 ሺህ ወጣቶች ስራ ይፈልጋሉ ብለዋል።

ወጣቶቹ በመስኖ፣ በእንስሳት እርባታ፣ በኮንስትራክሽን፣ በማዕድን፣ በማኑፋክቸሪንግና በየአካባቢያቸው ለስራ ዕድል አመቺ በሆኑ የሥራ ዘርፎች እንዲሰሩ እንደሚደረግ ነው ሃላፊው የተናገሩት።

እንደ አቶ ጎይቶም ገለጻ ከሥራ አጥ ወጣቶች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ቋሚ የሥራ ዕድል የሚፈጠርላቸው ሲሆኑ፥ ወደ ሥራ ለሚሰማሩ ወጣቶችም 408 ሄክታር የመስሪያ ቦታ ተዘጋጅቷል።

 

ምንጭ፡- ኢዜአ