በአዲስ አበባ በቀን ገቢ ግምቱ ከሚካተቱ ነጋዴዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት መረጃ ተሰብስቧል

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ በቀን ገቢ ግምት ይካተታሉ ከተባሉ 142 ሺህ 500 ነጋዴዎች መካከል ከግማሽ በላይ ነጋዴዎች መረጃ ተሰብስቧል።

የኢትዮጵያ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን ዛሬ በሰጠው መግለጫ እስካሁን የ75 ሺህ 551 ነጋዴዎችን የቀን ገቢ አጥንቻለሁ ብሏል።

ባለስልጣኑ የቀን ገቢ ግምቱ አፈጻጸም አሁን ላይ 53 በመቶ ደርሷል ነው ያለው።

የቀን ገቢ ግምቱ ባለፉት 23 ቀናት የተከናወነ ሲሆን፥ የቀሪ ነጋዴዎች ጥናት እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ እንደሚጠናቀቅም ባለስልጣኑ ገልጿል።

የቀን ገቢ ግምቱ በየሶስት አመቱ መካሄድ ቢኖርበትም ከታሰበው ዘግይቶ በስድስት አመቱ ነው የተካሄደው።

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጉዳዩ በቂ ትኩረት ባለመስጠታቸው ምክንያት መዘግየቱን፥ በባለስልጣኑ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ድጋፍና ክትትል ዳይሬክተር አቶ አትክልት ገብረእግዚአብሄር ተናግረዋል።

በቀጣይ በተቻለ መጠን የቀን ገቢ ግምቱ በየሶስት አመቱ እንደሚካሄድም ነው የተናገሩት።

ግምቱ ሲጀመር በነጋዴዎች ዘንድ ይስተዋል የነበረው፥ እቃ የማሸሽና የመደበቅ አዝማሚያ አሁን ላይ እየቀነሰ መምጣቱንም ባለስልጣኑ አስታውቋል።

የቀን ገቢ ግምት ጥናቱ ተጨማሪ ግብር ለመጣል ሳይሆን በመረጃ ላይ የተመሰረተ የግብር ስርዓት እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን ባለስልጣኑ ገልጾ ነበር።

ለቀን ገቢ ግምቱ 2 ሺህ የሚደርሱ ገማች ባለሙያዎች እና የምርመራ ቡድን ወደ ስራ የገቡ ሲሆን፥ ጥናቱ በግንቦት ወር ተጠናቆ ሰኔ ወር ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በመቀበል፤ ሀምሌ ወር ላይ ጥናቱ አዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ ላይ ተካቶ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

 

 


በዳዊት በጋሻው