ሀገሪቱ የምትገነባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ገቢ ማመንጨት እስከሚችሉ ድረስ የሚበደረው ብድር በዝቅተኛ ወለድ እንደሚሆን መንግስት ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ሀገሪቱ የምትገነባቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ገቢ ማመንጨት እስኪችሉ መንግስት የሚበደረው ብድር በዝቅተኛ ወለድ ብቻ እንደሚሆን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ገልጿል።

ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያ የብድር መጠን ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ አንጻር መካከለኛ የሚባል ሲሆን፥ ወደ ዝቅተኛ ደረጃ ለማውረድ መንግስት የሚፈጽመውን ብድር በዝቅተኛ ወለድ ብቻ ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን አብራርቷል።

የዓለም ባንክ መረጃ አንድ ሀገር የአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርቷን 56 በመቶ ያህል ብድር ቢኖርባት፥ ኢኮኖሚዋ ለአደጋ የማይጋለጥ በመሆኑ ብድር ማግኘት እንደሚቻል ያሳያል።

በዚህ መስፈርት ኢትዮጵያ እስካሁን የብድር መጠኗ ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርቷ አንጻር ከ30 በመቶ የማይበልጥ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገሪቱ የብድር ደረጃ ጤናማ የሚባል ነው።

በሌላ በኩል ሀገሪቱ በገባችው ውል መሰረት በ2009 ዓ.ም ለሀገር ውስጥ አበዳሪዎች 5 ቢሊየን ብር ለውጪ ደግሞ 6 ቢሊየን ብር በጥቅሉ 11 ቢሊየን ብር ብድር መመለስ መቻሏ የመበደር አቅሟን ያሳድገዋል።

የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ ሀገሪቱ ብድርና እርዳታን እያገኘች ነው ብሏል።

በ2009 በጀት ዓመትም ከመንግስታት ትብብርና ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት በብድርና እርዳታ መልክ ቃል የተገባው የገንዘብ መጠን 98 ነጥብ 876 ቢሊየን ብር ሲሆን፥ ፍሰቱ 78 ነጥብ 832 ቢሊየን ብር ነው።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሀጂ ኢብሳ በ2010 በጀት ዓመት ከሀገሪቱ በጀት 20 ነጥብ 2 ቢሊየን ብሩ በብድር የሚሸፈን በመሆኑ የመክፈል አቅምን ለማሳደግ መታቀዱን ተናግረዋል።

ይህም ለሀገር ውስጥ 7 ቢሊየን ብር ሲሆን፥ ለውጪ ደግሞ 9 ቢሊየን ብር ብድር በውሉ መሰረት የሚከፈል ይሆናል።

ሀገሪቱ የብድር መጠኗ 23 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ሆኖ መካከለኛ ተበዳሪ የደረሰች ሲሆን፥ በዚህ ከቀጠለ ወደ ከፍተኛ ተበዳሪ ሀገር ስለምትሰለፍ በዝቅተኛ ወለድ የብድር አሰራር እንዲቀጥል ተደርጓል።

ዳይሬክተሩ ሂደቱ ሀገሪቱ የያዘቻቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው በራሳቸው ብድር የመክፈል አቅም እስኪፈጥሩ የሚቀጥል ነው ብለዋል።

አሰራሩ ከዚህ በተጓዳኝ ወደ ውጪ የመላክ አቅም በሚፈለገው ደረጃ እስኪያድግ እንደሚቆይ ነው የተነገረው።

ብድርና እርዳታውን በዚህ ሁኔታ ከማስተናገድ ጎን ለጎን በ2010 አዲሱ የፋይናንስ ስርዓት አስተዳደር በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።

አሰራሩ ስኬቶች እየታዩበት መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፥ ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየባቸው 36 ተቋማትና ኦዲተሮች የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ነው ያሉት።

ሀገሪቱ በፈጣን እድገት ላይ የምትገኝ በመሆኗ ይህን አጠናክሮ ለማስቀጠል በፋይናንሱ ላይ የተሻሉ አሰራሮችን በመዘርጋት ውጤታማ አፈጻጸሞች እንዲኖሩ እንደሚሰራ ተነግሯል።

 

 

 

 


ኃይለኢየሱስ ስዩም