ምርት ገበያው በሃምሌ ወር የ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ምርት አገበያየ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 5 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሃምሌ ወር የ1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ምርት ማገበያየቱን አስታወቀ።

ምርት ገበያው በበጀት አመቱ የመጀመሪያ ወር 13 ሺህ 927 ቶን ቡና፣ 12 ሺህ 660 ቶን ሰሊጥ እና 1 ሺህ 850 ቶ ነጭ ቦሎቄ ማገበያየቱን አስታውቋል።

በወሩ ካገበያያቸው ምርቶች ቡና በመጠን የ49 ነጥብ 01 በመቶውን የምርት ድርሻ ሲይዝ፥ የ70 ነጥብ 96 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዳለውም ምርት ገበያው ለጣቢያችን በላከው መግለጫ ጠቅሷል።

ከምርቶች ዋጋ አንጻር መጠነኛ ጭማሪ መታየቱን የጠቀሰው መግለጫው፥ ከሰኔው ወር ጋር ሲነጻጸር በቡና የ1 ነጥብ 39 በመቶና በሰሊጥ 13 ነጥብ 2 በመቶ ጭማሪ ታይቷል ብሏል።

ከዚህ ውስጥ ወደ ውጪ የተላከ ቡና በመጠን የ68 ነጥብ 13 በመቶውን ድርሻ እንዲሁም የ69 ነጥብ 16 በመቶ የገቢ ድርሻ ማበርከቱንም መግለጫው ያመለክታል።

በወሩ 7 ሺህ 841 ቶን ያልታጠበ ቡና ለገበያ ቀርቦ 467 ሚሊየን ብር ገቢም ተገኝቷል ነው።

ከስፔሻሊቲ ቡና ደግሞ 131 ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱን ምርት ገበያው በመግለጫው አስታውቋል።

በወሩ ለአለም ገበያ ከቀረበው ምርት በተጨማሪም 2 ሺህ 635 ቶን ቡና ለሃገር ውስጥ ገበያ መቅረቡንም ገልጿል።

ከቡና ባለፈም በወሩ ለውጪ ገበያ ከቀረበ 12 ሺህ 660 ቶን ሰሊጥ 317 ሚሊየን ብር መገኘቱንም የምርት ገበያው መግለጫ ያመለክታል።