በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች 90 በመቶው ግብር ከፍለዋል

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 5 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ 59 ሺህ በላይ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች መካከል ከ53 ሺህ በላዩ የሚጠበቅባቸውን ግብር መክፈላቸውን የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ 59 ሺህ 275 የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ይገኛሉ፤ ከስድስት አመታት በኋላ የተካሄደውን የቀን ገቢ ግምት ተከትሎ ከእነዚህ ግብር ከፋዮች መካከል 60 በመቶው ግምቱን ተቀብለው ከሀምሌ አንድ ጀምሮ ግብራቸውን በመክፈል አሳልፈዋል።

ቀሪዎቹ 40 በመቶ የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮች ግን የቀን ገቢ ግመታው በዝቶብናል ከገቢያችን ጋር አይመጣጠንም በሚል ቅሬታ በማቅረባቸው ቅሬታቸው ሲታይ ቆይቷል።

ቅሬታ ካቀረቡት ግብር ከፋዮች መካከልም 42 በመቶዎቹ እንዲሻሻልላቸው፣ የ58 በመቶዎቹ ደግሞ ባለበት እንዲጸና በመወሰን 99 በመቶውን ቅሬታ ማስተናገዱን ባለስልጣኑ ገልጿል።

በዚህ ሂደት እስከ ሃምሌ 30 ባለው መደበኛ የግብር መክፈያ ጊዜም ከጠቅላላው ግብር ከፋዮች 80 በመቶው ግብራቸውን በተቀመጠው ጊዜ ሲከፍሉ፥ 20 በመቶው በተቀመጠው ጊዜ መክፈል ባለመቻላቸው የመክፈያ ጊዜው እስከ ነሃሴ አስር እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል።

እስካሁን በደረጃ “ሐ”ከተመዘገቡት ግብር ከፋዮች መካከል እስከ ትናንት ድረስ፥ 90 በመቶው ግብራቸውን መክፈላቸውን በባለስልጣኑ የግብር ከፋዮች ትምህርትና ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ በላይ ተናግረዋል።

በግብር መክፈያ ማዕከላት ተዘዋውረን ያነጋገርናቸው የደረጃ “ሐ” ግብር ከፋዮችም የተራዘመውን የግብር መክፈያ ጊዜ ተጠቅመው ያለ ቅጣት ግብራቸውን መክፈል እንደቻሉ ገልጸዋል።

ይሁን እንጅ ከዚህ በተቃራኒው ለቅሬታቸው ተገቢውን ምላሽ ስላላገኙ እስከ ዛሬ ግብራቸውን ያልከፈሉ ነጋዴዎችም ይገኛሉ፤ ግብር ከፋዮቹ እንደሚናገሩት ለወረዳ ላቀረቡት አቤቱታ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አልቻሉም።

ባለስልጣኑም እስካሁን የተራዘመውና የፊታችን ረቡዕ የሚጠናቀቀው የግብር መክፈያ ጊዜ፥ ተጨማሪ ቀናት ማራዘም ሳያቀስፈልግ ቅሬታዎቹን እና ክፍያውን ማስተናገድ እንደሚቻል ገልጿል።

 

 

በሀይለሚካኤል አበበ