በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑ 10 ሺህ ወጣቶች ልየታ መጠናቀቁ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ በመጀመሪያ ዙር የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑ 10 ሺህ ወጣቶችን የመለየት ስራ መጠናቀቁ የትግራይ ክልል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኤጀንሲ አስታውቋል።

የኤጀንሲው ኃላፊ አቶ ጥላሁን ታረቀ በሰጡት መግለጫ፥ በቅርቡ በተመረቀው ኢንዱስትሪ ፓርክ የስራ ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን በመጀመሪያ ዙር የተመለመሉት ወጣቶች በክልሉ ከሚገኙ 52 ወረዳዎች የተውጣጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የምልመላ መመዘኛውን አልፈው የተመረጡ ወጣቶች በተያዘው ወር፥ በዘርፉ ሙያዊ ስልጠና ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ እንዲገቡ ይደረጋል ነው ያሉት።

ከዚህ በተጨማሪ በመልካም ስነ-ምግባር፣ በሥራ ባህልና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ግንዛቤያቸውን የማሳደግ ሥራ በኤጀንሲው በኩል እንደሚሰራ ኃላፊው ገልጸዋል።

በሁለተኛው ዙር የስልጠና መርሃ ግብር በሚሰማሩባቸው የሥራ ዘርፎች በቴክኒክና ሙያ ክህሎት ያተኩሩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

በፓርኩ ውስጥ በሚገኙ ባለሃብቶች በተለይ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ በማሽን ኦፕሬተርነት፣ በልብስ ቅድና ስፌት፣ በዲዛይን ስራና በሌሎች ዘርፎች ተጨማሪ ስልጠና እንደሚሰጣቸው አመልክተዋል።

የመቀሌ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ የግንባታ ሥራው ተጠናቅቆ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በይፋ መመረቁ ይታወሳል።

ፓርኩ በ75 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው፡፡

የመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሙሉ በሙሉ ወደ ማምረት ሥራ ሲገባ 20 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች አዲስ የሥራ ዕድል እንደሚከፍት፥ የፌደራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አበበ አ በምረቃው ወቅት መግለጻቸው ይታወሳል።

 

 

 

 

ምንጭ፡-ኢዜአ