በባንኮች የኤሌክትሮኒክስ ካርዶችን የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር 6 ነጥብ 3 ሚሊየን ደርሰዋል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ባንኮች የኤሌክትሮኒክስ ካርዶችን የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር 6 ነጥብ 3 ሚሊየን መድረሱ ተገለፀ።

ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው የኤቲኤም ካርድ ተጠቃሚዎች ቁጥር በየዓመቱ በ66 በመቶ እድገትን እያሳየ መጥቷል።

በዚህም የደምበኞች ብዛት 2007 ዓ.ም ከነበረው የ2 ነጥብ 3 ሚሊየን ተጠቃሚዎች ቁጥር ሲነነፃፀር ከፍተኛ እድገትን ማሳየቱ ተነግሯል።

የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥርም እድገትን እያሳየ መምጣቱ ነው የተጠቆመው።

ከሁለት ዓመት በፊት 526 ሺህ የነበሩት የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ቁጥር በየዓመቱ በአማካይ የ117 በመቶ አድገትን በማሳየት አሁን 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ደርሰዋል።

የዚህ ዋና ምክንያትም የንግድ ባንኮች ቅርጫፎቻቸውንና ተቀማጫቸውን በየዓመቱ በተቀመጠላቸው ግብ መሰረት እያሳደጉ መሆናቸው ተጠቁሟል።

በካሳዬ ወልዴ