የኬኛ ቤቬሬጅ ግንባታን ለማፋጠን ከእንግሊዙ ግዙፍ ኩባንያ ጋር ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2010 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል በኬኛ ቤቬሬጅ ፋብሪካ ስር የሚቋቋሙ ተቋማትን ዕውን ለማድረግ ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል የግልና የመንግስት የኢኮኖሚ ጥምረት እና በኢንግሊዙ ካፒታል 54 ኩባንያ መካከል ተፈረመ።

ስምምነቱን የጥምረቱ ሰብሳቢ አቶ አባ ዱላ ገመዳና የኩባንያው ተወካይ ተፈራርመዋል።

ካፒታል 54 በዘርፉ ከፍተኛ ልምድና የገንዘብ አቅም ያለው ተቋም በመሆኑ በግንባታ ላይ ከውጭ ምንዛሪ ጋር ሊያጋጥም የሚችል እጥረትን ይፈታል ተብሎ እንደሚታመን በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

በተጨማሪም የካበተ የቴክኖሎጂ አቅም ያለው በመሆኑ የሚገነቡት የመጠጥ ፋብሪካዎች ዘመናዊ መሳሪያ እንዲጠቀሙ ያግዛልም ነው የተባለው።

ኬኛ ቤቬሬጅስ የተሰኘ ግዙፍ አክሲዮን ማህበር በግል ባለሀብቶች፣ በህዝብና በመንግስት ጥምረት ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነው የተመሰረተው።

የማህበሩ የአክስዮን ሽያጭ የተጠናቀቀ በመሆኑ የምስረታ ክፍያ መፈጸሙን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ተናግረዋል።

የቦርድ አመራር ምርጫም በቅርቡ እንደሚካሄድ ነው የታወቀው።

ኬኛ ቤቬሬጅ የክልሉ መንግስት፣ ህዝብና ባለሃብቱን አስተባብሮ የሚመራው የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት አካል ነው።