የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሩብ ዓመቱ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ብድር መስጠቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 2 ነጥብ 25 ቢሊየን ብር ለተጠቃሚዎች በብድር መስጠቱን አስታወቀ።

ልማት ባንኩ ለተጠቃሚዎቹ የሰጠው በሩብ ዓመቱ ለማበደር ካቀደ 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ውስጥ ሲሆን፥ አፈጻጸሙ የእቅዱን ግማሽ ያህል መስጠቱን ያመለክታል።

ልማት ባንኩ የሀገሪቷን የኢንዱስትሪ ልማት ለመደገፍና ለማበረታታት ፈጣን የብድር አገልግሎት ለመስጠት ፖሊሲዎቹንና መመሪያዎቹን በመፈተሽና በመከለስ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግም ነው የተጠቀሰው።

በባንኩ የስትራቴጂ ፕላንና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ክፍሌ ኃይለኢየሱስ፥ ልማት ባንኩ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 4 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ብድር ለመስጠት አቅዶ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።

ብድሩን ለመስጠት ያቀደውም ለግብርና፣ ለማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ ለማዕድንና ኢነርጂ፣ ለአነስተኛና መካከለኛ ሊዝ ፋይናንስ ግዥ አቅርቦትና ለሌሎች ዘርፎች መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ለግብርና ዘርፍ በብድር ከቀረበው 420 ሚሊየን ብር ውስጥ 117 ሚሊየን ብር እንዲሁም ለማምረቻው ኢንዱስትሪ ከተመደበው 2 ነጥብ 9 ቢልየን ብር የብድር አቅርቦት 1 ነጥብ 3 ቢልዮን ብር ብቻ ስራ ላይ መዋሉም ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ በሩብ ዓመቱ ከባለሃብቶች የቀረበው የብድር ጥያቄ አነስተኛ መሆን ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛነት በምክንያትነት እንደሚቀመጥ ነው ያመለከቱት።

በተጨማሪም ደንበኞች በብድር ጥያቄ ሂደት መረጃዎችን አሟልተው አለማቅረባቸው፣ የመሰረተ ልማት አለመሟላት፣ የብድር ጠያቂዎች ፕሮጀክት መለዋወጥና የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ለአፈፃፀሙ ዝቅተኛ መሆን ተጠቃሽ ነው።

ባንኩ በሩብ ዓመቱ ለመሰብሰብ ካቀደው የ1 ነጥብ 34 ቢሊየን ብር ተመላሽ ብድር ውስጥ 1 ነጥብ 21 ቢሊየን ብሩን አስመልሷል።

ምንጭ፦ ኢዜአ