ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ ንግድ የምታደርገውን ድጋፍ ወደ 200 ሚሊየን ፓውንድ አሳደገች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1፣ 2010 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ብሪታኒያ ለኢትዮጵያ ንግድ የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ ወደ 200 ሚሊየን የእንግሊዝ ፓውንድ ማሳደጓን አስታወቀች።

የብሪታኒያ ዓለም አቀፍ ንግድ ዋና ፀሃፊ ዶክተር ሊያም ፎክስ፥ የኢትዮጵያ እና yብሪታኒያ የሁለትዮች የንግድ ግንኙነትን ለማሳደግ ሀገሪቱ ለኤክስፖርት ፋይናንስ የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ በእጥፍ ማሳደጓን ይፋ አደርገዋል።

ዶክተር ፎክስ ከብሪታንያ ከተወጣጡ የንግድ፣ የመሰረተ ልማት እና የኢነርጂ ዘርፍ ልኡካን ጋር በኢትዮጵያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ነው ይህንን ያሉት።

በብሪታኒያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድ እንቅስቃሴ እድገት እያስመዘገበ ሲሆን፥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 የነበረው የንግድ ልውውጥ የ15 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር (439 ሚሊየን የእንግሊዝ ፓውንድ) ሆኖ ተመዝግቧል።

ዶክተር ፎክስ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታም ብሪታንያ ለኢትዮጵያ ኤክስፖርት የምታደርገው የገንዘብ ድጋፍ ወደ 200 ሚሊየን የእንግሊዝ ፓውን ወይም ወደ 7 ቢሊየን ብር ማደጉን አስታውቀዋል።

ይህም ከዚህ በፊት ሀገሪቱ ታደርግ የነበረው የገንዘብ ድጋፍ ላይ 3 ነጥብ 5 ቢሊን ብር የሚጨምር መሆኑንም አስታውቀዋል።

የገንዘብ ድጋፉም ወደ ኢትዮጵያ ምርቶቻቸውን ለሚልኩ የብሪታኒያ ኩባንያዎች እና የብሪታኒያ ምርቶችን እና አገልግሎቶችን ለሚገዙ ኢትዮጵያውያን የመድህን እና የብድር አገልግሎት የሚውለውን ድጋፍ የሚያካትት ነው

ዶክተር ፎክስ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጎብኝተዋል።

እንዲሁም በእንግሊዝ ኩባንያ የተቋቋመውን የፒታርድስ አዲስ የጫማ ፋብሪካ መርቀው የከፈቱ ሲሆን፥ ኩባንያው ለ1 ሺህ 500 ሰዎች የስራ እድል ፈጥሯል።

እንዲሁም ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና ከሌሎች ሚኒስትሮች ጋር የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር በሚቻልበት ዙሪያ ላይ መምከራቸው ተነግሯል።

ዶክተር ፎክስ ጉብኝታቸውን በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያም፥ የብሪታኒያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።

 

ምንጭ፦ www.gov.uk